የመድረክ አመራሮች በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር፤ የተሳካ ውይይት አደረጉ

መስከረም ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ አመራሮች በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር፤ ትናንትና እሁድ መስከረም 27 ቀን የተሳካ ውይይት አደረጉ።

ላለፉት 3 ሳምንታት ከሲያትል ጀምረው በአትላንታና ዴንቨር እንዲሁም ሚኒያፖሊስ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ስብሰባ ሲያደርጉ የቆዩት፤ የመድረክ ከፍተኛ አመራር አባላት፤ ፕ/ር መረራ ጉዲና፤ አቶ ስዬ አብርሀ፤ አቶ ተመስገን ዘውዴና አቶ ገብሩ አስራት በስብሰባው ላይ ተገኝተው የመድረክን አጀንዳዎች አስረድተዋል።

አቶ ስዬ አብረህ የአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ አመራር ስለሚጠበቅበትና መውሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች፤ እንዲሁም የአቶ መለስ መወገድ በኢህአዴግ ውስጥ ስለፈጠረው የማይሞላ ክፍተት፤ አቶ ተመስጌን ደሳለኝ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስለላበት መሰረታዊ ችግር፤ ፕረ/ር መረራ ጉዲና በውጭና በአገርቤት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የፖለቲካ ድርጅቶች ተባብረው መስራት ስለሚገባቸው ሁኔታ፤ እንዲሁም አቶ ገብሩ አስራት በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ከተሰብሳቢው ህዝብ ለተነሱት የግልና የጋራ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል።

ውይይት ከመጀመሩ በፊትና በውይይቱ መሀል፤ የኢህአፓ ወጣት ክንድ አባላት፤ በተለይ ለአቶ ስየ አብርሀ እሳቸው የሕወሀት ጦር አዛዥ በነበሩበት ሰዓት ተማርከው የደረሱበት ስለማይታወቅ የኢህአፓ ታጋዮች ሁኔታና፤ እሳቸው ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት፤ በኢህአዴግ ስለተፈጸሙ ጉዳቶች ተጠይቀው፤ ስልጣን ላይ በነበሩበት ሰዓት እንደኢህአዴግ ብዙ ጉዳቶች እንደተፈጸሙ አምነው፤ ሀላፊነት ወስደዋል።

ይቅርታ ስለመጠየቅ ጉዳይ ግን ይቅርታ ሰጪውም ነሺውም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ፤ ፍትሀዊ ስርአት ከመሰረትን በሁወላ የምናየው ነው ብለዋል።

ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ እሳቸውም በደርግ 6 አመት እንደታሰሩ፤ ወንድማቸውም እንደተገደለባቸው፤ ደርግ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶን ተባብለው ተቧድነው እንደተጋደሉ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ሰዓት የ40 አመት ፋይል አውጥተን ሂሳብ ማወራረድ ከጀመርን ግን፤ ኢህአፓን ጨምሮ ሁሉም ስለተነካካ፤  የወደፊቱን ላይ ብናተኩር ይሻላል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ፤ የባህር በር፤ የመሬት ፖሊሲና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ የመድረክ አመራሮች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል።

ተመልካቾቻችን፤ የስብሰባዉን ሙሉ ሂደት እንደደረሰ እናቀርባለን።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide