የመንግስት ጋዜጠኞችና መድረክ መወዛገባቸው ተሰማ

ጥር 23 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የውዝግቡ መንስኤ  መድረክ ባለፈው ዓርብ  አዲሱን የሊጅ አዋጅ በመቃወም በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመንግስትና የ ኢህአዴግ ድርጅት ልሳናት ጋዜጠኞች ከ ዋናው አጀንዳ  በመውጣት ፦”ሰሞኑን  አፋር ውስጥ በአሸባሪዎች  የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ -መንግስት የያዘውን አቋም ትደግፋላችሁ?ወይስ  ትቃወማላችሁ?” የሚል ጥያቄ  አከታትለው በመጠየቃቸው ነው።

ጋዜጣዊ መግለጫውን እየሰጡ የነበሩት የመድረክ አመራሮችም  በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች የየመጡበትን የሚዲያ ተቋማት ይገልጹላቸው ዘንድ ጠየቁ።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ ድርጅት፣ እና ባለቤትነታቸው የህወሃት የሆኑት የራዲዮ ፋና እና የዋልታ ጋዜጠኞችም በመተጋገዝ፦ “በጥያቄና መልስ ላይ የመጣንበትን ተቋም መመልከቱን ትታችሁ ለጥያቄያችን ብቻ መልስ ስጡን፤ ከየትም መጣን ከየትም እኛ ጋዜጠኞች ነን” ሲሉ ለመድረክ አመራሮች ማስፈራሪያ መሰል ተቃውሞ አሰሙ።

በዚህን ጊዜ የመድረክ የአመራር አባላት ዶ/ር መረራ ጉዲና፦ “እናንተ የመንግሥት ጋዜጠኞች እኮ እንደ ካድሬ አስተኳሽ ሆናችሁ። የኢህአዴግን ጥያቄዎች መጠየቃችሁን አቁማችሁ የጋዜጠኝነት ሙያና  ሥነ ምግባር  የሚፈቅደውን ሕዝባዊ ጥያቄ በንጽህና እንድትጠይቁ- በሕዝብ ገንዘብ የቀጠራችሁ ኢህአዴግ  ኖሮ፤ እኛም ራሳችንን ለመከላከል ወደዚህ ዓይነት ግንኙነት ባልገባን፤ ለኛም እዝኑልን” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበርና የመድረክ የአመራር አባል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው ፦“እውነት ለመናገር የእናንተ ሥራ የጋዜጠኝነት አይደለም። ለኢህአዴግ ግብዓት የሚሆነውን መርጣችሁ የተልዕኮ ሥራ ነው የምትሠሩት፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና አዲስ ዘመን ፤ የእኛን ሙሉ መግለጫ በትክክል ለሕዝብ አታቀርቡም፡፡ በአድሏዊነት ትቆራርጡታላችሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምንናገረውን ሳይሆን፤ እጃችን ሲወራጭ እያሳያችሁ ሌላ ታወራላችሁ”  በማለት በቁጣ ወቅሰዋል።

“አብዛኛው ኢህአዴግ በሚሰራቸው እንደ አኪልዳማ አይነት ፕሮፓጋንዳዎች የሚታዩት ምስሎችና የሚሰሙት ድምጾች እናንተ ዜና ለመስራት በሚል መጥታችሁ የቀረፃችሁዋቸውና እንደሚመቻችሁ ያበጃጃችሁዋቸው ናቸው”ያሉት ዶክተር ነጋሶ፤  “ኢህአዴግ ስማችንን የሚያጠፋው፣ ክስ የሚመሰርትብን፡፡ እናንተ አንድነት ቢሮ መጥታችሁ ያነሳችሁትን ድምጽና ምስል  እየተጠቀመ አይደል እንዴ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ዶ/ር ነጋሶ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፦ “እኛ ፤የፕሬስ ነጻነትን ባንደግፍና ዴሞክራቶች ባንሆን ኖሮ፤ እናንተ የምትሰሩትን ሥራ በማየት ብቻ ሁለተኛ በቢሯችን እንዳትገኙ ማድረግ እንችል ነበር። ነገር ግን ለምን እንደምትጠቀሙበት እያወቅን እንኳ፤” ለታሪክ ይቅረብ” በሚል ነው  ዝም ያልናችሁ እንጂ እንደ እናንተ ስራማ እዚህ እንድትገቡ አያስፈልግም ነበር” በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡

የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር ሞርጋ ፉሪሳ  በበኩላቸው፦“ዛሬ ለጋዜጣዊ መግለጫ በአጀንዳ የጠራናችሁ፤’ የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር’ ስንል በመሬት ዓዋጁ ላይ በማተኮር ነው፤ እናንተ ግን ሆን ብላችሁ የኢህአዴግን የተንኮል አጀንዳ ይዛችሁ፤ ሰሞኑን በአፋር የተካሄደውን እገታ ታወግዛላችሁ አታወግዙም፣ ሕገመንግስቱን ትለውጣላችሁ?ወይስ አትለውጡም? ትላላችሁ። ይዛችሁት የመጣችሁትን የተልዕኮ ጥያቄ  አቁማችሁ በተያዘው አጀንዳ ላይ ብቻ እንደ ጋዜጠኛ ጥያቄ ካላችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ”ሲሉ ተናግረዋል።

በኢዲቲንግ ስም የሰዎችንም ሆነ የድርጅቶችን ሀሳብ ቆራርጦ  ያልተባለንና የተዛባን መልዕክት ማስተላለፍ፤ ጠቅላላ ሀሳብን ላለማስተላለፍ ከመከልከል የከፋ ወንጀል እንደሆነ የገለጹ አንድ ከፍተኛ የመድረክ አባል ፤ከዚህ አንፃር የሰዎችን ቃልና ምስል እንደፈለገ እየደራረተና እየቆራረጠ  በማስተላለፍ የቆሸሸ ተግባር ላይ የተሰማራው ኢህአዴግ፤-ጠቅላላ ሚዲያን ከማይፈቅደው ደርግ የከፋ አገዛዝ ነው ማለት እንደሚቻል አመልክተዋል።