የመሰረታዊ የሸቀጣሸቀጦች እጥረት በበአሉ አከባበር ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነዋሪዎች ገለጹ

ኢሳት (ታህሳስ 28 ፥ 2009)

ሰሞኑን በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የተፈጠረው የመሰረታዊ የሸቀጣሸቀጦች እጥረት በበአሉ አከባበር ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነዋሪዎች አስታወቁ።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በዘይት ዱቄትና ስኳር ምርቶች ላይ የታየው አቅርቦት እጥረት በበአሉ ወቅት ሊቀርፍ አለመቻሉን ተጠቃሚዎች የገለጹ ሲሆን፣ የከተማዋ የንግድ ቢሮ በበኩሉ እጥረቱ ከስርጭት ጋር በተገናኘ የተፈጠረ ነው ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

ይሁንና አስመጪ ነጋዴዎች በሃገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነጋዴዎች የፈለጉትን ሸቀጣሸቀጥ በተፈለገው መጠን ሊያስገቡ እንዳላስቻላቸው ይገልጻሉ።

በመሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦች ላይ የተከሰተውን እጥረት ተከትሎ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱን የሚናገሩት ተጠቃሚዎች ችግሩ ለበዓሉ አከባበር ወቅት ዕልባት አለማግኘቱና ልዩ ትኩረት ማጣቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙን አስረድትተዋል።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሃገሪቱ ምግብ ነክ ያልሆኑ የሸቀጣሸቀጥ የዋጋ ግሽበት በህዳር ወር ከ8.1 ወደ 8.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።

የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ እያሳዩ መምጣታቸውን ተከትሎም የባለፈው ወር የዋጋ ግሽበት ከ5.6 በመቶ ወደ 7 በመቶ ማደጉን ኤጀንሲው በቅርቡ ባወጣው ወርሃዊ ሪፖርት አመልክቷል። አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሃገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ንግድ ማሽቆልቆልና የውጭ ምንዛሪ ክምችት መቀነስ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል ሲሉ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የአለም ባንክ በበኩሉ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ የፖሊሲ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባት አሳስቧል።