የመለስ መንግስት ጋዳፊ እንዲህ አይነት አሳዛኝ እጣ ከመድረሱ በፊት ለውጥ እንዲያደርጉ መክረናቸው ነበር ሲል መግለጫ ሰጠ

ኢሳት ዜና:- የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃል አቀባይ አቶ ደና ሙፍቲ እንደተናገሩት ” ገና ከመሰረቱ የሊቢያ አደባባዮች በህዝብ ሳይጥለቀለቁ ፣ ደም ፈሶ ህይወት ሳይጠፋ፣  የሙአመር ጋዳፊ የ42 አመታት ቤተሰባዊ አገዛዝ እንዲበቃ የህዝብ ጩህት ጆሮ እንዲያገኝ ሊቢያውያን ከሰብአዊነት ተሽረው አይጦች ሲባሉ ኢትዮጵያ ይህ አካሄድ እንደማያዋጣና ጋዳፊ ከመፍትሄ ይልቅ የችግሩ አካል መሆናቸውን ስትገልጽ  ቆይታለች” ብለዋል።

ቃለ አቀባዩ “ጋዳፊ  የኢትዮጵያንም ሆነ የሌሎች ሀገራትን ጥሪ በተለመደው ንቀታቸውና የማን አለብኝ ሰሜት ነበር ከቁብ ሳይቆጥሩት በጆራ ዳባ ልበስ ብሂላቻው የገፉበት።  የሙአመር ጋዳፊ ያረጀ እርዮተ አለም ወራትን ያስቆጥር እንጂ አመት አልደፈነም።  የህዝብ ማእበልና ጥያቄ በአጭሩ መልሱን አገኘ ይህም ተምሳሌነቱ ለሌሎችም ጭምር ነው ” ብለዋል።

ቃል አቀባ  ኢትዮጵያ ቀደም ብላ ከናይጄሪያጋር በመሆን ለሽግግር መንግስቱ እውቅና ሰጥታ በጋራ እንደ አዲስ ተባብራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት መግለጿንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አቋም የከተሞች የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጧል። “ኢትዮጵያ ደም ሳይፈስ የህዝብ ጩሀት እንዲሰማ ጋዳፊን ስትመክር ነበር በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር መናገሩ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን የህዝብ ጩሀት ሳይሆን የሌለውን የህዝብ ጩሀት ሲያዳምጥ መክረሙን የሚያሳይ ነው “የሚል አስተያየት መስማቱን ዘጋቢያችን ገልጧል።

ለዘጋቢያችን አስተያየቱን የሰጡ አቶ ሰለማኢ መኩሪያ የተባሉ የአንድነት አባል  “በርግጥም እነዚህ ሰዎች አስቂኞች ናቸው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እያለ ያለው መለስ ጋዳፊን ሳይሆኑ ቶሎ ብለው ለውጥ ያምጡ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጩሀት ይህ ነው። እነመለስ እራሳቸው እየተመከሩ መካሪ ሆነው ሲገኙ ነገሩን ሁሉ አስቂኝ ያደርገዋል። የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ ይህን የሚናገሩት ለጋዳፊ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ለህወሀት ባለስልጣናት ይመስላል” ብለዋል።