የሆስተሷ የአበራሽ ኃይላይን ሁለት ዓይኗን አጥፍቶ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰባት ተጠርጣረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡

ኢሳት ዜና :- ሆስተስ አበራሽ ለህክምና ከሄደችበት ባንኮክ- ታይላንድ ከሁለት ሣምንት በኋላ እንደምትመጣ በአቃቤ ህግ የተገለጸ ሲሆን ሁለቱም ዓይኖቿ መቶ በመቶ የማየት ተስፋ እንደሌላቸው ከሀኪሞቿ እንደተነገራትና በጭንቅላቷ፣ በሰውነቷና በእጆቿ ላይ ያደረሰባት ከባድ ጉዳትን በመታከም ላይ ነች ሲሉ አጎቷ አቶ አስመላሽ ሞላ ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡

 የአቃቤ ህግ የክስ ቻርጅ እንደሚያስረዳው በመዝገብ ቁጥር 112 ሺ 331 አቶ ፍሰሃ ታደሰ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1 እና 539/1/ሀ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ሰው ለመግደል በማሰብ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክ/ ከተማ ወረዳ 14 ክልል ገርጂ ቁጥር 5 ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ የግል ተበዳይ አበራሽ ኃይላይ በምትኖርበት መኖሪያ ቤቷ ውስጥ እያለች ስልክ በመደወል ሊያገኛት እንደሚፈልግ ገልጦላት ነበር።

 ባለቤቷ ቤቷ ድረስ በመሄድ አብረው ቤት ውስጥ ከቆዩ በኋላ የወግ ቁጥሩ ኤም ፒ 09472 እስታርተር ሽጉጥ በማውጣት ተበዳይ ላይ በመደቀን አስፈራርቶ እንድትቀመጥ በማድረግ ጉሮሮዋን አንቆ በሽጉጥ ደጋግሞ ጭንቅላቷን በመደብደብ ተበዳይ ስትወድቅ፣ ምንነቱ ያልታወቀ ስለት ነገር ከኪሱ በማውጣት ዓይኗን ደጋግሞ በመውጋት እና ዓይኗን ጎልጉሎ በማውጣት ተበዳይ ተዝለፍልፋ ስትወድቅ የሞተች መስሎት ራሱን ለፖሊስ አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ በፈጸመው ከባድ የሰው ግድያ ሙከራ ወንጀል ተከሷል፡፡

 በሁለተኛነትም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 809 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የወግ ቁጥሩ ኤም ፒ 09472 እስታርተር ሽጉጥ ከአምስት ጥይቶች ጋር ሳይፈቀድለት ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈጸመው የተከለከለ ጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ተከሷል ይላል የአቃቤ ህግ የክስ ቻርጅ፡፡

 ተከሳሽ ችሎት በሚቀርብበት ጊዜ በማኅበር የተደራጁ በርካታ ሴቶች  እና የተወሰኑ ወንዶች አፋጣኝ ፍርድ ይሰጠን፣ ፍትህ እንፈልጋለን በማለት በህብረት ድምፃቸውን ማሰማታቸው ታውቋል፡፡