የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ በብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ሊመክር ነው

(ኢሳት ዜና–መስከረም 22/2010) የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ህወሃት/ማዕከላዊ ኮሚቴ በብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር በመቀሌ ነገ መወያየት እንደሚጀምር ተገለጸ።

ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብአዴን፣ደኢህዴንና ኦህዴድ በሕወሃት የተቀመጠላቸውን ድክመት እንዲያርሙ በተሰጣቸው አጀንዳዎች ላይ ግምገማ ሲያደርጉ ሕወሃት ግን በብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል።

በሕወሃት ስብሰባ ላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያልሆኑ የቀድሞ ከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች ይሳተፋሉ ተብሏል።

በእድሜና በተለያዩ ምክንያቶች ከህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰናበቱትን አንጋፋ የህወሃት አመራሮችን ያካተተው ስብሰባ ከመስከረም 22 ጀምሮ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በስብሰባው ሕወሃት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዴት እንደመራው ግምገማ እንደሚካሄድ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ በድረ ገጹ እንዳመለከተው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚመለከታቸው እጀንዳዎች የድርጅትና መንግስት የ2009 አፈጻጸም፣ በጥልቅ ተሀድሶ የነበረውን ጠንካራና ደካማ ጎን በመገምገም ተጠናክሮ የሚቀጥልበት አቅጣጫ ማስቀመጥና የቀጣይ የ2010 ትኩረት አቅጣጭዎችን እንደሚያስቀምጥ አመላክቷል።

በሌላ በኩል ከሳምንት በፊት በባህርዳር ግምገማ ያካሄደው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አምስት ገዳይና ተላላፊ ፖለቲካዊ በሽታዎች የተባሉት የርዕዮተ አለም መስመር ክህደት፣የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ተግባር፣የትምክህት ተግባርና አመለካከት፣የአቅም ውስንነትና ስር የሰደደ አድርባይነትና ጸረ ዲሞክራሲ መሆናቸውን ጽሕፈት ቤቱ አሳውቆ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከመስከረም 2 እስከ 5/2010 ባደረገው ግምገማ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን የውስጠ ድርጅት አጀንዳዎች ላይ ማተኮሩን ለማወቅ ተችሏል።

የደኢህዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ በሰጡት መግለጫ ደኢህዴን በጎሰኝነት፣በጎጠኝነትና በመንደርተኝነት ሃሳብ የሚያራምዱ ጎታችና ኋላቀር የሆኑ ከፋፋይ አመለካከቶችን በመገምገም የተግባር ርምጃ መውሰድ መጀመሩን ገልጸዋል።

ህወሃት ሀገራዊ እቅድና አቅጣጫ በሚነድፍበት ይህ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰናበቱትን አቶ ስብሀት ነጋ፣አቶ ስዩም መስፍንን ጨምሮ ሌሎች አንጋፋ ካድሬዎችን ሊያሳትፍ እንደሚችል የደረሰን መረጃ አመላክቷል።