ዓባይ ግድብ የደረሰበትን ደረጃ በመቶኛ የመግለጽ ፍለጎት እንደሌላቸው የፕሮጀክቱ ሃላፊዎች ተናገሩ

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን የግድቡን ምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ለጉብኝት የተጋበዙ የህብረተሰቡ ክፍሎችና ጋዜጠኞች፤የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ በመቶኛ የመግለጽ ፍላጎቱ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
የግድቡን ምስረታ በዓል በከፍተኛ ፌሽታ ለማክበር ላይ ታች የሚለው የህውሃት /ኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት ከተለያዩ ሚዲያዎችና ከቻግኒ ከተማ የተሰባሰቡ የስርዓቱ ደጋፊዎችን በማስጎብኘት ስለግድቡ ስራ መቀጠል ለማስረዳት ቢሞክሩም የግድቡ ስራ ግንባታ በታለመለት መልኩ እንዳልቀጠለ ለመታዘብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በግድቡ ወስጥ በመስራት ላይ ያሉት ሰራተኞች ቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን እና ውስን ማሽነሪዎችን ሲንቀሳቀሱ ማየታቸውን የገለጹት ጎብኝዎቹ የግድቡ ስራ ባለፈው ዓመት ከነበረበት ደረጃ በጉልህ የሚታይ ለውጥ እንደሌለው ታዝበዋል፡፡የግድቡ ስራ በአጀማመሩ ላይ የነበረውን ሙቀት ይዞ ለመጓዝ ያልቻለው ለግድቡ ስራ የሚቀርበው ማንኛውም ቁሳቁስ ከህውሃት ድርጅቶች ብቻ እንዲቀርብ መደረጉና ለህውሃት ሰዎች ትርፋማ በሆነው የሚቴክ ድርጅት አብዛኛው ስራ ያለውድድር በከፍተኛ ገንዘብ እንዲሰራ መደረጉ እንደሆነ ጎብኝዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የቦንድ ሽያጭ ለማከናዎን የሞከሩ የባንክ ባለሙያዎችም እንደገለጹት በቦንድ ሳምንቱ የተጠበቀውን ያህል ግዥ ባለመፈጸሙ ከፍተኛ ወቀሳ ደርሶባቸዋል፡፡
የመንግስት አመራሮች በባህርዳር ዲስትሪክት ስር በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች እንዲሸጥ የተላከው ሃያ ሚሊዮን ብር ቢሆንም አንድ አራተኛውም አለመሸጡን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የባህርዳር ዲስትሪክት ባንክ ባለሙያዎች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
በባህርዳር ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የወጣት ሊግ ተወካዮችና አመራሮች ከቦንድ ሽያጩ ሳምንት በኋላም ቤት ለቤት በመዞር ነጋዴዎችን ቦንድ እንዲገዙ እንዳስገደዷቸው የሚናገሩት የንግዱ ማህበረሰብ ዓባላት በከተማዎች ከሚታየው የቀዘቀዘ ንግድ እንቅስቃሴ በላይ ገንዘብ እንዲያወጡ መገደዳቸውን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡
“በግድቡ ላይ ያለን ጥያቄ አልተመለሰም” የሚሉት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለግድቡ የሚደረገው መዋጮ ለተፈለገው ዓላማ በአግባቡ እንደማይውል ጥርጣሬያቸው የበዛ ነው፡፡ ከአሁን በፊት የህውሃት መንግስት የአባይን ግድብ ያካለለ ካርታ አውጥቶ ይፋ ማድረጉ በቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቅሬታ ያሳደረ
በመሆኑ በግድቡ የቦንድ ሽያጭ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመገኘቱ ከዚህ የመነጨ እንደሆነ ያምናሉ፡፡