”ዋልድባ በትግራይ ክልል የሚገኝ በመሆኑ፤በልማታችን ላይ ጥያቄ ማንሳት አትችሉም” በማለት አንድ የትግራይ ክልል የደህንነት መኮንን ተናገረ

መጋቢት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመኮንኑ ንግግር የተበሳጩት ብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ ፦”ዋልድባ የትግሬው ወይም የአማራው ብቻ አይደለም።ዓለማቀፍ ገዳማችን ነው”ሲሉ ገስፀውታል።

ብአዴን/ኢህአዴግ በዋልድባ ጉዳይ ከመነኮሳቱና ከ አካባቢው ነዋሪ ጋር ለመነጋገር ሰሞኑን በጎንደር ከተማ በጠራውና በሥኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጁ በ አቶ ዓባይ ፀሀዬ በተመራው ስብሳባ ላይ በርካታ ተቃውሞ ከመንፀባረቃቸውም ባሻገር ውይይቱ ያለስምምነት መቋጨቱ ታውቋል።

በተለይ የስብሰባው መሪ አቶ አባይ ፀሀዬ  በርካታ ጥያቄዎችን እያድበሰብሱ ስላልተጤቋቸው ነገሮች ሲናገሩ መታየታቸው ብዙሀኑን ተሰብሳቢ ማስቀየሙ ተሰምቷል።

በተደጋጋሚ፦”ቅዱስነቱ ሳይነካ በነበረ ይዞታው ይቀጥላል፤መንግስት ፈፅሞ የገዳሙን ይዞታ አይነካም” ሲሉ የተደመጡት አቶ ዓባይ፤ እየተነሳ ስላለው የቅዱሳን አጽምና ወደ ውስጥ 500 ሜትር ተገብቶ ስለታረሰው መሬት መልስ  ሳይሰጡ አልፈዋል።

በዚህም ምክንያት በፍፃሜው  ለመነበብ የተዘጋጀው የ አቋም መግለጫ ሳይነበብ ስብሰባው ተጠናቋል።

ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ከስብሰባው መንፈስ ውጪ የሆነ ሪፖርት አቅርቧል ያሉት ተሰብሳቢዎቹ፤ በስብሰባው ያልተገኙት የቤተ-ምናሴ መነኮሳት ጭምር በስብሰባው እንደተገኙ ጭምር ተደርጎ መዘገቡ እጅግ አሳዝኖናል ብለዋል።

የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  በጎንደር የተካሄደውን  ስብሰባአስመልክቶ ባስተላለፈው በዚሁ ዜና ዋልድባም፤ የስኳር ፋብሪካው የሚገነባበት አድርቃይ ወረዳም በትግራይ ክልል እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል።

በያዘው የቅርስና የብራና መፃህፍት መጠን ከ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከ ዓለም ጭምር አንደኛ እንደሆነ የሚነገርለት የዋልድባ ገዳም፤ ቀደም ባሉት ሥርዓቶች በወሎና በጎንደር  ክፍላተ አገር ድንበር አቅራቢያ እንደሚገኝ በርካታ የጂኦግራፊና የታሪክ መረጃዎች  ያመለክታሉ።

የአድርቃይ ወረዳም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጎንደር አካል መሆኑ ይታወቃል።

ይሁንና ህወሀት መራሹ መንግስትና ብዙሀን መገናኛዎቹ ፦ዋልድባም፤አድርቃይም በትግራይ ክልል ያሉ ይዞታዎች ናቸው በማለት በተደጋጋሚ እየገለጹ ይገኛሉ።

ከዚህም ባሻገር  አንድ የትግራይ ክልል የደህንነት መኮንን፤በዋልድባ መታረስ ተቃውሞ እያሰሙ ያሉትን መነኮሳትና የጎንደር ነዋሪዎች “ዋልድባ በትግራይ ክልል ስለሚገኝ፤ በልማታችን ላይ ጣልቃ መግባት አትችሉም” በማለት በመናገሩ፤ በስብሰባው ላይ ከነበሩት ብዙዎቹ  በጩኸትና በቁጣ ደህንነቱን ዝም እንዳሰኙት ታውቋል።

በመኮንኑ ደህንነት የተበሳጩት የሀገረ-ስብከቱ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤልሳዕም፦”ዋልድባ የትግሬውም ብቻ፤ የአማራውም ብቻ አይደለም!ዓለማቀፍ ገዳማችን ነው” በማለት ገስጸውታል።

“ዋልድባም፤አድርቃይም በትግራይ የሚገኝ ነው ካሉ፤የጎንደርን ነዋሪ ማባበል ለምን ፈለጉ?” ብለዋል አንድ  በኢትዮ-ቲዩብ ላይ ከተለጠፈው ከኢቲቪ ዜና ግርጌ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰብ።

ግለሰቡ አያይዘውም፦”ነገሩ ሆድ ሲያውቅ፤ዶሮ ማታ ነው፤ እንኳን እነ ዋልድባ፤እነ ሁመራም የየትኛው ክልል እንደሆኑ ገዥዎቻች ያውቁታል”ብለዋል።

ቀደም ሲል ሁመራን ከጎንደር ተነጥሎ በትግራይ ክልል መካተቱ፤ ራስ ዳሸንም በትግራይ ክልል እንደሚገኝ የሚያሳይ የመማሪያ መጸህፍት መሰራጨቱ፣ ቀደም ሲል የወሎ ግዛት የነበሩት አላማጣና ዋግ ወደ ትግራይ ክልል መጠቃለላቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide