ወደ የመን ከሚሰደዱት ስደተኞች ውስጥ 80 በመቶ ኢትዮጵያውን መሆናቸውን ተመድ አስታወቀ

የካቲት ፩ ( አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለዓመታት በእርስበርስ ጦርነት ወደምትታመሰው የመን የሚሰደዱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር /UNHCR/ ፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከገቡት 87 000 ስደተኞች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ወይም ከ69 600 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሎአል። ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የሚይዙት ሶማሊያውያን ስደተኞች ናቸው።
በኢትዮጵያ ተከታታይ እድገት ተመዘገበ እየተባለ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በእየለቱ ቢለፈፍም፣ የአረብ አገራትን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ከመቀነስ ይለቅ ሲጨምር ይታያል።
በኬንያ በኢትዮጵያ ድንበር ፣ በሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር እንዲሁም በጅቡቲና በሲማሊያ አካባቢዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ግብጽና አውሮፓ ለመጓዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አማራጮችን እየጠበቁ ነው።