ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በእስር ላይ የሚገኙት የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ኢትዮጵያውያን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል አማካኝነት ደብዳቤ እንዲጽፉ ጠየቁ

ኢሳት ዜና:- የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን በአምነስቲ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “በፌስቡክና በቲዊተር ዘመን ደብዳቤ መጻፍ አያስፈልግም የሚሉ ሰዎች የእኔን የእስር ዘመን እንዲያስታውሱ እመክራቸዋለሁ” ብለዋል።

“እኔ  ነጻ እሆናለሁ የሚል ተስፋ አልነበረኝም። እኔ ምንም ወንጀል ሳልፈጽም ሀሳቤን በነጻነት በመግለጼ ብቻ ነበር የታሰርኩት ።  የኢትዮጵያ መንግስት ተቀናቃኞችን ለእስር በመዳረግ ተቃውሞን ለማፈን የሚችል ይመስለዋል” ያሉት ወ/ት ብርቱካን  አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2009 እኔ እንድፈታ ህዝቡ ደብዳቤ እንዲጽፍ ባስተባበረበት ወቅት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ደብዳቤ  ጽፈውልኛል ብለዋል።

በብቸኝነት  በታሰርኩበት ወቅት የእናንተ ደብዳቤ ብቸኛ መጽናኛየ ነበር የሚሉት ወ/ት ብርቱካን፣ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምስጋና ይግባውና  ነጻነቴን ለመቀዳጀት በቅቻለሁ አክለዋል።

ሌሎችም  የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ኢትዮጵያውያን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል አማካኝነት ደብዳቤ እንዲጽፉ ወ/ት ብርቱካን መክረዋል።