ክረምቱ ሲገባ የአረቡ አብዮት ወጀብ ወደ ኢትዮጵያ እየነፈሰ ነው ሲል ረዩተርስ ዘገበ

ህዳር 29 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የረዩተርሱ ጆን ሊዮልድ ባቀረበው ሰፊ ዘገባ በአረቡ አለም የተጀመረው ህዝባዊ ማእበል ፣ ወደ ጥንታዊቷ የስልጣኔ ማእከል ፣ ኢትዮጵያም፣  እየገሰገሰ ነው።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር  አቶ መለስ ዜናዊ ካለፈው የሰኔ ወር ጀምሮ ተቃዋሚዎችን፣  ጋዜጠኞችን እና የሲቪል ማህበረሰብ አባላትን ማዋከብ ፣ ማሰርና አገር ጥለው እንዲሰደዱ ማድረጋቸውን ረዩተርስ ገልጣዐል።

በቅርቡ የስደትን ጎራ ከተቀላቀሉት መካከል የሲፒጄ የነጻነት ተሸላሚ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ አሳታሚ ዳዊት ከበደ  እንደሚገኝበት እንዲሁም ባለፈው ወር በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ይገኝ የነበረው መምህር የኔሰው ገብሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ጭቆና በመቃወም ራሱን ማቃጠሉንም ኢሳትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የየኔሰው አሟሟት የቱኒዚያዊውን ሙሀመድ ቡአዚዝን መንገድ የተከተለ መሆኑን እና ድርጊቱ በውጭ አገራት የሚገኙ ድረገጾችን ማጣበቡንም አስታውሷል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ለረዩተርስ የገለጠው የአዲስ ነገር ጋዜጣ መስራች  አብይ ተክለማርያም “የኔሰው ገብሬ እራሱን ማቃጠሉ ልዩ ነገር መሆኑን፣ በኢትዮጵያ እራስን በእሳት የማቃጠል ልምድ እንደሌለና ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን ለማስከበር እስከምን ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉና ችግሩ ምን ያክል እንደጎዳቸው ያመለክታል” ብሎአል።

አብይ አያይዞም፣ ለኢትዮጵያ እርዳታ የሚለግሱት አሜሪካና እንግሊዝን የመሳሰሉ አገሮች  ለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ትኩረት እንደማይሰጡ፣ ይልቁንም የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረቱ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንጅ ሰብአዊ መብት ማክበር አለመሆኑን ሲገልጥ ለጋሽ አገሮች ” አዎ” ብለው የተቀበሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሷል።

በኢትዮጵያ  መንግስት እና በተቃዋሚዎች መካከል መቀራረብ ለመፍጠርና ምርጫ ለማካሄድ ይቻል እንደሆነ ረዩተርስ ጥያቄ ያረበላቸው የግንቦት7 ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ” እንዲህ አይነቱ ነገር እንደማይፈጠር ይልቁንም መንግስት የሚዲያ እና የጸረሽብረተኝነት ህጎችን በማውጣት ተቃዋሚዎችን  ለእስር እና ለስደት እየዳረገ” መሆኑን ተናግረዋል።

“በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስትን ማሸነፍ አይቻልም፣ ህዝቡ ሆ ብሎ መነሳት ይኖርበታል፤ መንግስትም አንድ ነገር እየመጣ መሆኑን ያውቃል፤ መቼ እንደሚደርስ እርግጠኛ መሆን ግን አልቻለም ”  ሲሉ አቶ ኤፍሬም አክለዋል።

አብይ በበኩሉ መንግስት የማህበራዊ የመገናኛ ብዙሀንን ሆን ብሎ እንዲኮላሹ በማድረጉ የኢትዮጵያ ሊህቃን እርስ በርሳቸው እንዳይገናኙ፣ ህዝቡም ስለ አረብ አብዮት እንዳይሰማ መደረጉን ገልጧል።

ጆን ሊዮልድ ባቀረበው አስተያየት በደቡቡ የአፍሪካ ክፍል የሚገኙ  መሪዎች፣ የአረቡ አብዮት ወደ አካባቢያቸው እንዳይመጣ የሚፈልጉት፣ ስልጣንን ከሀብትና ከህይወት ጋር ስለሚያያይዙት ነው ብሎአል።

የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን አጡ ማለት ሀብታቸውን፣ ሲበረታ ደግሞ   እንደጋዳፊ ህይወታቸውንም ሊያጡ  እንደሚችሉ የሚገልጠው ጆን፣  የኢትዮጵያ መሪዎችም ይህን በመፍራት እንዲህ አይነት ተቃውሞ ሊያነሳሱ ይችላሉ ብለው የሚጠረጥሩዋቸውን ሰዎች ሁሉ ማሰርን መርጠዋል ብሎአል።

የጋዳፊ እጣ ፈንታ  የሚያስተምረው ነገር ቢኖር ጭቆናን ማስፋፋት መፍትሄ አለመሆኑን ነው የሚለው ጆን፣ መፍትሄው ነጻ ሀሳብን እንዲንሸራሸርና ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲያብብ መፍቀድ ብቻ ነው ሲል መክሮአል።

አሁን የሚታየው አፈና ለአጭር ጊዜ ሊጠቅም ይችል ካልሆነ በስተቀር ለረጅም ጊዜ የሚጠቅም መፍትሄ አለመሆኑን ገልጦ ፣ የኢትዮጵያ መሪዎችና የአፍሪካ መሪዎች ” ዛሬ ወደ ክረምቱ የገባን ቢመስላቸውም፣ ነገ ጸደይ ተመልሶ እንደሚመጣ ማወቅ ግድ ይላቸዋል”  ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠይቆ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከመብት እጦትና ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ፣ ህዝቡ የመንግስት ለውጥ እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።

ከየኔ ሰው ገብሬ ሞት በሁዋላ በርካታ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ያለውን ጭቆና እያነሱ በመጻፍ ላይ ናቸው።