ኩማ ደመቅሳ በጀርመን የሚኖሩ የሃይማኖት አባቶች የዲያስፖራውን ተጽእኖ የሚቀንስ ስራ እንዲሰሩ ጠየቁ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ ባለፈው የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በጀርመን የሚኖሩ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር ቀረቤታ ያላቸውን ነጋዴዎችና ግለሰቦች በመሰብሰብና ከፍ ያለ ግብዣ በማድረግ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ላይ የሚያደርሱትን ተጽእኖ ለመቋቋም የሚያስችል ስብከት እና ሌሎችንም ስራዎች እንዲሰሩ አዘዋል።
ቅዳሜ ቀን ለሃይማኖት አባቶች ብቻ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ ከወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እና ከእስልምና የተወከሉ የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል። አቶ ኩማ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር አውለነዋል፣ ነገር ግን እዚህ በውጭ ያለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር እንድታግዙን፣ እንድትመክሩን ነው የጠራናችሁ ብለዋቸዋል።
በውይይቱ ላይ በጀርመን የሲኖዶሱ ተወካይ የሆኑት አባ ሙሴ የኢህአዴግን መንግስት በማሞገስ ረጅም ንግግር አድርገዋል። የአባ ሙሴ ረጅም የውዳሴ ንግግር ያሰለቻቸው የሚመስሉት አቶ ኩማ፣ እንድትመክሩን ነው የጠራናችሁ በማለት ለአባ ሙሴ ንግግር ቀዝቃዛ መልስ ሰጥተዋል። አባ ሙሴ ለሚነሱት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ሲሰጡ መዋላቸውንም ስብሰባውን የተከታተሉ ምንጮች ገልጸዋል።
ከኦርቶዶክስ ቤ/ክ አንድ አባት ብቻ “ብዙ ኢትዮጵያውያን እና ቤተክርስቲያኖች እያሉ ለምን እኛን ብቻ ትጠራላችሁ፣ ደግሞስ ህገመንግስቱን እናከብራለን ትላላችሁ፣ ህገመንግስቱ ይከበር ብለው የሚጠይቁ አይደሉም ወይ የሚገደሉት የሚል “ ጥያቄ ሲጠይቁ፣ ከሙስሊም ተወካዮችም አንድ አባት ጥያቄ አቅርበዋል። ሌሎቹ ግን 4 ሰአት በፈጀው ስብሰባ ላይ ምንም ሳይናገሩ ስብሰባው ተጠናቋል።
ከስብሰባው በሁዋላ የህወሃት አባል እንደሆኑ በሚነገርላቸውና በቅርቡ በፍራንክፈርት ምግብ ቤት በከፈቱት አቶ መላኩ አስተናጋጅነት ከፍ ያለ የምሳ ግብዣ ተደርጓል።
የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም ፣ ስለሉአላዊነትና ስለኢትዮጵያ ትልቅነት እንዲሁም ስለ ህዳሴው ግድብና ይህ መንግስት ስለሰራው የልማት ስራ እንዲሰብኩ ሶስት መመሪያዎች ተሰጥቷቸዋል።
ተመሳሳይ ስብሰባዎች በየ6 ወሩ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚደረጉ ሲገለጽ፣ የህወሃት ቀረቤታ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አባ ሙሴ፣ ስድስት ወር ይበዛል፣ በየሶስት ወር መሆን አለበት፣ እዚህ ላይ ብዙ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።
በሚቀጥለው ቀን ደግሞ በፍራንክፈርት አካባቢ ሱቆች ያሉዋቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱ ሰዎች የተጠሩ ሲሆን፣ በዚሁ ስብሰባ ላይ አቶ ኩማ ዲያስፖራውን ለምን ዝም ትሉታላችሁ፣ እየወጣ ሲሰለፍ ፣ ይህ መንግስት ያመጣውን ሰላም ሲያበላሽ እያያችሁ ወይ የማግባባት ስራ ወይ የመገዳደር ስራ መስራት አለባችሁ ብለዋል።
ተሰብሳቢዎቹ በእያካባቢያው በዲያስፖራው ላይ ስራ እንዲሰሩ መመሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ እንዲህ አይነት ስብሰባዎች በየአገራቱ እንደሚካሄድ ተነግሯቸዋል። ለእነሱም እንዲሁም ከፍተኛ የምሳ ግብዣ ተደርጎላቸዋል።
የሁለቱም ስብሰባዎች አላማ ዲያስፖራው በኢህአዴግ ላይ የጀመረውን ዘመቻ አቁሞ መንግስትን እንዲደግፍ ለማድረግ እንደነበር በስብሰባው የተሳተፉ ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን አፈና፣ እስርና ግድያ በመቃወም እንዲሁም ዲያስፖራውን ለማፈን የሚደረገውን ሩጫ ለማውገዝ በፍራንክፈርት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቅዳሜ ኤፕሪል 1 የእግር ጉዞ እንደሚያደርጉ ታውቋል።
የእግር ጉዞው ጥቁር በመልበስ በሮይመር ፓላት ከ12 ኤ ኤም ጀምሮ እንደሚካሄድ የታወቀ ሲሆን፣ በኦሮምያ፣ አማራ ፣ በጋምቤላ እና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የሚደርሱ ጭፍጨፋዎችን ያወግዛል፣ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች እንዲፈቱ ይጠይቃል።