ከ400 በላይ የፖለቲካ እስረኞች ፍትህ አጥተው በመንገላታት ላይ ናቸው

ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከቃልቲና እና ከቂልንጦ ማረሚያ ቤቶች ለኢሳት በተላከው ስም ዝርዝር ላይ ለመመልከት እንደሚቻለው ፣ በሁለቱ እስር ቤቶች ብቻ በመለስ መንግስት የሀሰት ክስ ተከሰው ፍትህ አጥተው የሚሰቃዩ 401 ሰዎች አሉ። አብዛኞቹ የታሰሩት ከግንቦት7 እና ከኦነግ ጋር በተያያዘ ነው። በብሄር ተዋጽኦም አብዛኞቹ አስረኞች የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ናቸው።

በአቶ አንዱአለም መዝገብ 24፣ በአቶ በቀለ ገርባ 9፣ በጄ/ል ተፈራ ማሞ 46፣ በአቶ ተሻለ በኬ ፣ 69፣ በአቶ አል አህመድ ሰኢድ 33፣ በአቶ አሸናፊ አዱኛ 22፣ በአቶ ጌትነት ገመቹ 20፣ በአቶ ደጃሳ ወርቁ፣ 22 እና በአቶ ደበላ ጣፋ 35 እስረኞች ለአብነት ያክል ተጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከል 217 እስረኞች ከእድሜልክ እስከ 15 አመታት የተፈረደባቸው ሲሆን፣ 184ቱ ደግሞ እስካሁን ፍርድ አላገኙም። አብዛኞቹ እስረኞች የመገናኛ ብዙሀንንና አለማቀፉ ማህበረሰብ የማያውቃቸው ናቸው።

የመለስ መንግስት ለስልጣኑ የሚያሰጋውን ሁሉ ለእስር በመዳረጉ ዘወትር በአለማቀፍ ድርጅቶች ይወቀሳል።

ኢሳት በድረገጹ የፖለቲካ እስረኞችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደርጋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምናልባትም በሰኔ ወር ውስጥ የአውሮፓ ህብረት አንድ ጉባኤ ለማዘጋጀት እንዳቀደ ለማወቅ ተችሎአል። የኢሳት ታማኝ የዲፐሎማቲክ ምንጮች እንደሚሉት ህብረቱ በአለም ደረጃ ታዋቂ ከሆኑት እና ብዙ የማግባቢያ ( ሎቢ) ስራ ከሚሰራላቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ከመሳሰሉት እስረኞች በስተቀር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ እስረኞች መረጃ የለውም። በሰኔው ጉባኤ የእስረኞችን ስም ዝርዝርና ፎቶ በጉባኤ አዳራሹ ውስጥ ለማስቀመጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide