ከ20 ሺ በላይ ሰዎች የሞያሌን ግጭት በመሸሽ ኬንያ ገቡ::

ሐምሌ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-  ቢቢሲ ቀይ መስቀልን ጠቅሶ እንደዘገበው በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል በተነሳው ግጭት 18 ሰዎች ተገድለው 12 ደግሞ ቆስለዋል። ኢሳት ትናንት ከአካካቢው ሰዎች እና ከተለያዩ ድርጅቶች ባሰባሰበው መረጃ 20 ሰዎች መገደላቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የፌደራል ፖሊስ አባል መሆኑን፣ 7 የክልል ፖሊሶች መቁሰላቸውን ዘግቦ ነበር። ዛሬ በደረሰን ዘገባ ደግሞ የሟቾች ቁጥር 30 ደርሷል።

ከ20 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን የሶማሊ ተወላጅ በሆኑ ገሪዎችና የኦሮሞ ተወላጅ በሆኑ ቦረናዎች መካከል የተጀመረውን ግጭት በመፍራት ድንበር ተሻግረው ኬንያ ገብተዋል። የመንግስት ሀይሎች ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ ቢገቡም፣ ህዝቡ ግን አሁንም ወደ ኬንያ በመጉረፍ ላይ እንዳለ ነው የኬንያ ባለስልጣናት የሚናገሩት።

ግጭቱ ከመሬት ጋር የተያያዘ መሆኑን ቢቢሲ ቢጠቅስም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ግን የፌደራል ስርአቱ ውጤት ነው ይላሉ።

የታጠቁ ሚሊሺያዎች ጎራ ላይተውና መሽገው መዋጋታቸውን ግጭቱ ሞያሌ ከተማ ድረስ ደርሶ እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል።

ቀይ መስቀል ለስደተኞች እርዳታ ለማድረግ በመረባረብ ላይ ነው።

በትናንት ዘገባችን የሶማሊ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ሚሊሺያዎች በግጭቱ እጃቸውን ማስገባታቸው ፣ ለብዙዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በዛሬው እለት አንጻራዊ ሰላም ማግኘታቸውን፣ ይሁን እንጅ ግጭቱ ዳግም ያገረሻል በሚል ምክንያት እንደልባቸው ለመውጣት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide