ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ታንኮች ወደ አገር ገቡ

ሚያዝያ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሚያዚያ 24 ቀን 2009 ዓም ጠዋት በርካታ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ታንኮችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ሾፌሮች ገልጸዋል።
በጅቡቲ ወደብ 200 የሚሆኑ አዳዲስ ታንኮች የተራገፉ መሆኑን የሚገልጹት የአይን እማኞች፣ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ታንኮች የጫኑ ሎቤድ መኪኖች ወደ ደብረዘይት ተንቀሳቅሰዋል።
ከ7 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መራባቸው በተነገረ በሳምንት በእርዳታ እህል ፋንታ ይህን ያክል ቁጥር ታንክ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ግርምት እንደፈጠረባቸው ሾፌሮች ገልጸዋል።
ገዢው ፓርቲ በአገር ውስጥ ከገባበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ከኤርትራ ጋር ጦርነት ሊያደርግ እንደሚችል የተለያዩ ፍንጮች እየታዩ ነው። ምላሻቸው እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ የስራዊት ምልመላ ለማድረግ ተደጋጋሚ ማስታወቂያዎች መውጣታቸው እንዲሁም በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ እንከተላለን በመላት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ትግራይ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው ፣ አገዛዙ የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀየስ ሊጠቀምበት እንደሚችል ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።