ከግብር ጋር በተያያዘ ነጋዴዎች የሚያሰሙት ተቃውሞ ቀጥሎአል

ሐምሌ ፯ ( ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ መጠን ያለው ግብር እንዲከፍሉ የተጠየቁ ነጋዴዎች ተቃውሞቸውን በስብሰባ ቦታዎች ከመግልጽ አልፈው ወደ አደባባይ በመውጣት በማሰማት ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በአምቦ ትናንት ሃሙስ በተነሳው ተቃውሞ መኪኖች የተቃጠሉና የተሰባበሩ ሲሆን፣ በምስራቅ ሃረርጌ ደግሞ ከ3 ቀናት በፊት የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል። በፈዲስ፣ ጭሮ ( አሰበ ተፈሪ)፣ ሜታ ወረዳ እና ሌሎችም በርካታ ወረዳዎች ተቃውሞ መደረጉን ወኪላችን ዘግቧል። በወልቂጤ እረፋዱ አካባቢ ውጥረት ሰፍኖ ውሎአል።
በሃረር የሚገኙ ነጋዴዎችም እንዲሁ ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። በተለይ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ቀድሞ ከሚከፍሉት 5 እጥፍ እንዲከፍሉ መጠያቃቸውን የሚቀበሉት አልሆነም።
የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች እየተነሳ ላለው ተቃውሞ የሚሰጡት ምላሽ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው የሚሉት ነጋዴዎች፣ አንዳንዶች የምትችሉትን ክፍሉና ተከራከሩ ሲሉ ሌሎች ደግሞ በእቃዎቻቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ ይመክሩዋቸዋል። ከተለያዩ ባለስልጣናት የሚያገኙት እርስ በርሱ የሚጣረስ መልስ ነጋዴዎችን ግራ እያጋባ ነው።
በመላ አገሪቱ የሚታየው የንግድ እንቅስቃሴ በተደካመበት በዚህ ወቅት ነጋዴዎች የተጋነነ ግብር እንዲከፍሉ መደረጉ ወቅቱን ያላገናዘበ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪ ነጋዴዎች አሉ።