ከዎላይታ ዞን ወደ ሲዳማ ዞን በኃይል ለማካለል የተጀመረውን እንቅስቃሴ የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ዎህዴግ/ ተቃወመ

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዎህዴግ ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓም ባወጣው ባለ 4 ገጽ መግለጫ የዎላይታ ህዝብ ብዛትና የመሬት ጥበትን ተከትሎ የዎላይታ ወጣቶች በትምህርት መቅሰሚያ ዕድሜኣቸው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየሄዱ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮኣቸውን እየገፉ መሆኑን ጠቅሶ፣ በአካባቢው ያለው የመሬት ጥበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ጊዜ፣ አሁን ደግሞ ‹‹ ጮካሬ የሚባል የዎላይታ ይዞታ አካል የሆነ መሬትን ለአጎራባች ሲዳማ ዞን ለማስረከብ እንቅስቃሴ “ መደረጉ አስገራሚ ነው ብሎአል።
ድርጅቱ በመግለጫው ፣ ይህ ቦታ ቀደም ሲል መሬትን የህዝብ ካደረገው ከ1967 አዋጅ በኋላም በዎላይታ ይዞታ ሥር እንደሚገኝ ፣ በይዞታነት የተያዘው በጦርነት ወይም በድንበር መግፋት ያለመሆኑን ፣ ይልቁንም ሰላማዊና ጥንታዊ የህዝቦችን አሰፋፈር በጠበቀ መልኩ የተደረገ መሆኑን፣ ይህንም የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ የሲዳማ አዛውንቶችም አሳምረው እንደሚያውቁትና የሲዳማ ህዝብ፣ ‹‹አግባብነት በሌለው መንገድ ከዎላይታ መሬት ተቆርሶ ይሰጠኝ “ እንደማይል ገልጿል።
‹ይህ ህዝብ ካለበት ችግር ተላቆ የለማ ሕይወት የሚመራበትን መንገድ እየነቀሱና እየተገበሩ ማገዝ እንጂ ፣ተቃራኒውን ለመፈጸም እንዴት ይታሰባል ?›› ብሎ የሚጠይቀው መግለጫው፣ ‹‹እውነትን ረግጦ ሊጠቅመው የታሰበለት ወገንም ቢሆን ፣ጊዚያዊ የሆነ፣ ከአንገት በላይ ምሥጋና ቢቸር እንጂ ከውስጡ አያመሰግንም፡፡ ይልቅስ ሊታዘብ ይችላል፡፡›› በማለት የድርጊቱን ሙከራ ይተቻል፡፡
‹‹ ለምዕተ ዓመታት ፀንቶ የቆየውን የዎላይታ እና የሲዳማን የመግባባትና የመተጋገዝ ስሜት ከአስር ወይም ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ባልተጠበቀ ሁኔታ በተከሰተ ችግር ምክንያት እንዲሸረሸር ሁለቱም ወገኖች እንደማይፈቅዱ ሙሉ እምነት አለን፡፡›› ያለው መግለጫው፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለ የቆየና የዳበረ የወንድማማችነት አቋም ይበልጥ ተጠናክሮና ተከብሮ እንዲቀጥል ፣ የሁለቱም ዞኖች ነባር ድንበር ሳይሸራረፍ እንዲከበር፤ አለ የተባለ ችግርም ፍትሃዊነት በጠበቀ ሁኔታ ተፈቶ በአካባቢው የተሟላ የመልካም አስተዳደር መስፈን ሂደት እንዲረጋገጥ” ጠይቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ ለዞኖቹና ለአዋሳኝ ወረዳዎች አመራሮች በቤታቸው ጠርተው አካባቢው በአፋጣኝ እንዲካለል መመሪያ እንደሰጡ መዘገባችን ይታወሳል።
የአቶ ሃይለማርያምን ትዕዛዝ፡ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን የገዢው ፓርቲ የዞንና ወረዳ ካድሬዎችም አንቀበልም እያሉ ነው። ይህ አካሄድ በዎላይታ ህዝብና በሲዳማ ህዝብ መካከል አላስፈላጊ ችግር ከመፍጠር ባለፈ፣ በዎላይታ ህዝብ ሥም በመንግስት አመራር ላይ በተቀመጡ ባለሥልጣናት፣ በወላይታ ህዝብ ፣ አልፎም በወላይታ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና አባላት መካከልም ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ምንጮች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ባለፈው ሰኞ፣ ሰኔ 19 ቀን 2009 ዓም አቶ ተሾመ ቶጋ ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎችን በወላይታ ከተማ ሰብስበው የነበረ ሲሆን፣ ህዝቡ ያለፍርሃት የተቃውሞ ሃሳቡን ገልጿል። የመንግስት ባለስልጣናት ‹‹ ይህ የመንግስትን ትዕዛዝ አልቀበልም ፣ አልታዘዝም ማለት ነው፣ ያስጠይቃልም ›› በማለት ለማስፈራራት ቢሞክሩም ህዝቡ ከተቃውሞው አልተመለሰም ፡፡ ማክሰኞ በተደረገው ስብሰባም ሃሳባቸውን ካቀረቡት አስራ ስምንት ሰዎች መካከል ከሁለት የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በቀር ሁሉም ሃሳቡን ተቃውመዋል፡፡ በአብዛኛው የተቃውሞ ሃሳባቸውን ያቀረቡት የዎላይታ ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች መሆናቸውንና የዞንና ወረዳ ባለሥልጣናትና ካድሬዎችም ጉዳዩን በዝምታ እየተከታተሉ መሆኑን የስብሰባው ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
በስብሰባው ማጠቃለያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ‹‹ እነዚህ ሰዎች፣ ሲዳማዎች በተደጋጋሚ መሬቱን ጠይቀው ተከልክለዋል፤ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚ/ሩ ከእኛ ስለሆኑ ነው የተከለከልነው እያሉ ስሞታ እያሰሙ ነው፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ልናስወቅሳቸው አይገባምና መሬቱን መስጠት አለብን›› ባሉ ጊዜ አዳራሹ በጩኸት ተናግቷል፡፡
አንድ በዎላይታ ህዝብ ትግል የረጅም ጊዜ ተሳትፎ ያላቸው የዞኑ ነዋሪ ‹‹ ይህ የዎላይታን ህዝብ ማንነት ለማጥፋት ‹ ወጋጎዳ › የሚል ቋንቋ እስከመፍጠር ድረስ ተኪዶበት የከሸፈው ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ህዝቡ ይህን በማክሸፉና በወቅቱ በክልልና በማዕከል የነበሩ ባለስልጣናት ባደረባቸው ቂም እንዲሁም ህዝብ በምርጫ እነዚህን ሰዎች ድምጽ ስለነፈጋቸው የበቀል በትር መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ህዝቡን በአደባባይ ‹ይቅርታ › ቢጠይቁም ይህ ለሥልጣን ሲባል በህዝብ ላይ የተፈጸመ ክህደት በይቅርታ የሚታለፍ አይደለም በማለት የትውልድ አካባቢያቸውን ቀይረው ሁሉ በምርጫ ቢወዳደሩም በተደጋጋሚ በድምጹ ስለቀጣቸው ፣ እኛን ለሥልጣን ያበቃን ኢህአዴግ እንጂ ህዝባችን አይደለም ፣ ለዚህም ኢህአዴግ/ መንግስት የሚለውን ማንኛውንም ውሳኔ ማስፈጸም እንጂ ለህዝቡ ማሰብ-መጨነቅ የለብንም › ከማለት የመነጨ የቂም በቀል እርምጃ ነው ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ለውሳኔው ተፈጻሚነት እየተንቀሳቀሱ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ለተረሸኑ የሲዳማ ተወላጆች የአካባቢውን መሬት እንደ ደም ካሳ በመክፈል በዎላይታ ህዝብ የተነፈጋቸውን ድጋፍ ከሲዳማ ህዝብ ለማግኘት የጀመሩት ጥረት ይመስላል ሲሉ እኝሁ ግለሰብ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ‹‹ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ የቀን ሥራ ተሰማርተው የሚኖሩ የዎላይታ ወጣቶች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ታፍሰው ወዳልታወቀ ቦታ እየተጫኑ መሆኑ ›› በከተማዋ ውስጥ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው ቅርብ የሆኑ ምንጮች ፣ እርምጃው በትክክል እየተወሰደ እንደሆነ ፣ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው እንደተወሰዱባቸውና እነርሱም በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።