ከአማራ ክልል የተወከሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተቃወሙ

ጥቅምት ፲ (አሥር) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ተወካዮቹ አዋጁ አፋኝ በመሆኑ በክልላችን እንዲሰራ አንፈቅድም በማለት ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል። ተወካዮቹ የያዙትን አቋም እንዲለውጡ ከትናንት ጀምሮ በደህንነቶች ሲዋከቡ ውለዋል። ተቃውሞአቸውን ለመግለጽም የተዘጋጀላቸውን ምግብ ሳይመገቡ ቀርተዋል።

ይህ አፋኝ ህግ በክልላችን ህዝብ ላይ ተግባራዊ እንዲሆንና ከህዝብ ጋር እንድንጣላ አንፈልግም ያሉት ተወካዮቹ፣ አዋጁ እንዳይጸድቅ በጽኑ ተከራክረዋል። 137 የሚሆኑት የምክር ቤት አባላት በአንድ ድምጽ ያሳዩት ተቃውሞ ያልተጠበቀ ሲሆን፣ ትናንትና ዛሬ ከሌሎች አባላት ጋር ሳይገናኙ ለብቻቸው ተገልለው  ውለዋል። “ህዝብ ሲረገጥና ሲሞት ዝም ብለን አናይም፣ የመረጠን ህዝብ የእሱን መብት ልናስጠብቅለት እንጅ  በአዋጅ ልናስገድለው አይደለም” በማለት ጠንካራ አቋም መያዛቸው የአገዛዙን ከፍተኛ ሹሞች አስደንግጧል። የገዢው ፓርቲ ልሳናት ግን አዋጁ በሙሉ ድምጽ እንደጸደቀ ገልጸዋል።

አዋጁ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አገዛዙ በሙሉ ወታደራዊ ሃይሉ በመንቀሳቀስ በርካታ ዜጎችን ወደ እስር ቤት ወስዷል። በአንዳንድ ወረዳዎች ከ 1 ሺ በላይ ዜጎች ታስረው እንደሚገኙ የሚደርሱን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ኮማንድ ፖስት የተባለው አዲሱ ወታደራዊ ገዢ ሃይል ባለፉት 3 ቀናት  1 ሺ 600 ሰዎች ብቻ መታሰራቸውን ገልጿል። ይሁን እንጅ ባለፉት 3 ቀናት በ10 ሺ ዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኦሮምያ ክልል የኮማንድ ፖስት አባላት ሴቶችን እየደፈሩ እንዲሁም ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ለፖሊስ ሲያመለክቱ ለ6 ወር ያክል ምንም ስልጣን ስለማይኖረን ምንም ማድረግ አንችልም የሚል መልስ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። በአማራ ክልል ኮማንድ ፖስቱ የጦር መሳሪያ ለመቀማት እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ከአንዳንድ አርሶአደሮች ተቃውሞ ደርሶባቸዋል።

በጭልጋ ወረዳ ሻሀርዳ ቀበሌ ጥቅምት 14/2016 ዓም ቸሩ መንክር የተባለውን ጎልማሳ ከቤቱ ወደ ስራ ሲሄድ ገድለው ጠመንጃውን ወስደዋል ። የግለሰቡ የቀብር ስነስርዓት በማግስቱን ሸኸዲ አካባቢ የሚገኝ ማህበረ ስላሴ ገዳም  ተፈፀሟል ። ጥቅምት 19፣ 2016 ደግሞ ጭልጋ ወረዳ ሻሃርዳ ቀበሌ እያዩ ተረፈ የሚባል ጎልማሳ ቤት ወታደሮቹ  በምሸት ሰአት ቤቱን ሰብረው በመግባት ገለው መሳሪያውን ወሰደዋል። እያዩ በአካባቢው ህዝብ ዘነድ ከፍተኛ ከበሬታ እንደነበረው ምንጮች ገልጸዋል። በዚሁ ቀን አናጋው የተባለውን ሰው  ግደለው  መሳሪያውን ወስደውታል። የአካባቢውን ህዝብ ስለአንድነት በመስበክ  የሚታወቅ እንደነበር የሚገለጹት የአካባቢው ምንጮች፣ የቀብር ስነስርዓቱም ዛሬ ይፈጸማል።

የኮማንድ ፖስት አባላት ነን የሚሉ ሰዎች  ኢሳትንና ኦ ኤም ኤንን ታያላችሁ ያሉዋቸውን ሰዎች እየያዙ ማሰር የጀመሩ ሲሆን፣ በበርካታ ከተሞች ህዝቡ ዲሾችን እንዲያወርድ እያስፈራሩ ነው። ይሁን እንጅ ህዝቡ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አሁንም ኢሳትንና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃንን መመልከቱን ቀጥሎአል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ህዝቡ ዲሽ አናወርድም በማለት በእምቢተኝነቱ እንደ ጸና ነው።

በሌላ በኩል ጎንደር ከተማ ውስጥ ታሰረው የነበሩ በርካታ ወጣቶች ከ5 እስከ 100 ሺ ብር የዋስትና ገንዘብ እያስያዙ እንዲወጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፏል። ብዙዎቹ ወጣቶች መንገድ ላይ የታፈሱ ሲሆን፣ ምንም ወንጀል ሊገኝባቸው ባይችልም ገንዘብ አምጡና ውጡ መባላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።