ከሳኡዲ አረቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን እየተጉላሉ ነው

ግንቦት ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ሕገወጥ ስደተኞች ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ የውጭ አገር ዜጎች አገርቷን ለቀው በመውጣት ላይ ናቸው። የተለያዩ አገራት በኤንባሲዎቻቸውና በቆንስላዎች አማካኝነት ከቀረጥ ነጻ እቃዎቻቸውን እንዲያስገቡ ለዜጎቻቸው እገዛ እያደረጉ ነው። ፈቃደኛ ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ግን ወደ ኤንባሲዎቸው በመሄድ ለመመለስ ቢጠይቁም የጉዞ ሰነዶችን በአፍጣኝ ለማግኘት ተቸግረዋል። ልጆቻቸውን ሳኡዲ አረቢያ የወለዱ አንዳንድ ወላጆች እንዳሉት የዲኤንኤ ምርመራን ጨምሮ የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ቀናቶችን በማራዘም ለተለያዩ ወጪዎች መዳረጋቸውን በምሬት ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት የመጓጓዣ ዋጋና የእቃ መላኪያ ካርጎ ዋጋ በእጥፍ ጭማሪ አሳይቷል። በቅርብ ጊዜያት ወደ ሳኡዲ የገቡ ኢትዮጵያዊያን የትራንስፖርት መክፍል አለመቻላቸው ለከፍተኛ ጭንቀት ዳርጓቸዋል።
የኤንባሲውና ቆንስላው ሰራተኞች ውስጥ ለውስጥ ለተወሰኑ ዜጎች ጉዞዋቸው እንዲፋጠን በሚያደርጉት አሰራር ማዘናቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ተጓዦች አስታውቀዋል።
”በረመዳን ወር ጾም ምክንያት ድካም ላይ ብንሆንም የኤንባሲው ሰራተኞች ግን ምንም ዓይነት ሃዘኔታ ሳይኖራቸው በቀጠሮ ያመላልሱናል” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።