እየተካሄደ ያለው የነጋዴዎች አድማ እንደቀጠለ ነው

ሐምሌ ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ላለፉት 2 ሳምንታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲካሄድ የሰነበተው የነጋዴዎች አድማ ዛሬም ቀጥሎአል።
በታላቁ መርካቶ ገበያ ትናንት ሰኞ የተጀመረውን አድማ ለማስቆም ገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የደህንነትና የፖሊስ ሰራዊት በማሰማራት በነጋዴዎች ላይ ማስፈራሪያ ሲያደርግ ቢውልም፣ ዛሬም በተለያዩ አካባቢዎች መደብሮች ተዘግተው ታይተዋል። በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ቄራ የገበያ አዳራሽ ደግሞ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን በሃይል ለማስከፈት ከሄዱ ፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል። ነጋዴዎች በአቋማቸው በመጽናት ይህን ዜና እስካጠናከርንበት እስከ እኩለ ቀን ድረስ የንግድ ድርጅቶቻቸውን አልከፈቱም።
በመርካቶ ፖሊሶችና ደህንነቶች በየንግድ መደብሮች ላይ የማስፈራሪያ ወረቀቶችን በመለጠፍ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ለማስገደድ ቢሞክሩም፣ በራጉኤል፣ አስፋወሰን፣ አራተኛና አካባቢው፣ ዱባይ ተራ እንዲሁም
ከአዲስ አበባ ውጭ ደግሞ በሞጣ ፣ በጅማ፣ ሻምቡና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች አድማው ቀጥሎ ውሎአል።
በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎችም የዕለት ገቢ ግብር ውሳኔን በውጥረት እየጠበቁት ነው፡፡ አራት መቶብር ሽያጭ በቀን እንዳለው ለእለት ግብር ውሳኔ አጥኝዎች የተናገረው አነስተኛ የሞባይል ቤት ወጣት ነጋዴ፣ ለሪፖርተራችን እንደገለጸው ስራውን የጀመረው ከቤተሰብ ባገኘው ድጋፍና በግሉ በተማረው የጥገና እውቀት ቢሆንም የቀን ገቢ ገማቾች ግን እርሱ ያለውን ሳይሆን በግምት በሶስጥ ዕጥፍ በማባዛት፣ “ገቢ” በሚል በመመዝገባቸው ከፍተኛ ግብር ይጣልብኝ ይሆናል በሚል ስጋት ላይ ወድቋል።
አብዛኞቹን ነጋዴዎች ተዘዋውራ ያነጋገረችው ሪፖርተራችን ከባህር ዳር እንደዘገበችው በዚህ ዓመት በክልሉ በተከሰተው ህዝባዊ አመጽ ምክንያት ነጋዴዎች ገበያቸው ቀዝቅዟል፡፡በዚህ ሁኔታ እያሉ አዲስ የቀን ገቢ ግብር ግምት ለማጥናት መወሰኑ ነጋዴውን ማህበረሰብ ሆን ተብሎ ለመጉዳት የታሰበ ነው ሲሉ ነጋዴዎች ይናገራሉ።
ነጋዴዎች ምንም ሽያጭ በሌለበት ሁኔታ ከፍተኛ የዕለት ገቢ ግምት ከተጣለባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ዘጋቢያችን ገልጻለች።
በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በተደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ በግፍ ደማቸው ለፈሰሰው የባህር ዳር እና አካባቢ ነዋሪዎችን ለማስታወስ ከነሃሴ 1 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ለሶስት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ በሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲደረግ ጥሪ ተላልፏል፡፡
የደጀን ከተማ ነጋዴዎችም ከሃምሌ ከ19/2009 ዓ/ም ጀምሮ የንግድ ድርጅቶቸውን እንዲዘጉ መልዕክት እየተላለፈ ነው።