እንደ ኦሮምያና አማራ ሁሉ የደቡብ ክልል የመንግስት ሰራተኞችም በጥልቅ ተሃድሶ ስም የቀረበውን ሪፖርት ተቃወሙ

የካቲት ፪ ( ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን በጂንካ ከተማ በዞኑ የሚገኙ ሰራተኞች ጥልቅ ተሃድሶ ለማድረግ በሚል ከሰኞ ጥር 29 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ አዳራሽ እያደረጉት ባለው ስብሰባ ላይ ፣ ለውይይት መነሻ ሆኖ የቀረበውን ጽሁፍ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገውታል። የውውይት መነሻ ጽሁፉ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ከቀድሞ ስርአቶች ጋር ሲነጻጻር የተሻለ ድል ማስመዝገቡን ፣ ነገር ግን ህዝቡ ሲቪል ሰራተኛው በሚሰጠው አገልግሎት ሊረካ አልቻለም ፣ ከልማቱም ተጠቃሚ አልሆነም በሚል፣ ጥፋቱን ሁሉ ወደ ሰራተኛው ለመውሰድ የተደረገውን ሙከራ ሰራተኞች በአንድ ድምጽ ተቃውመውታል።
ሰራተኞች “ ስለምን ስለአለፈው ስርዓት ትነግሩናላችሁ፣ ስለምን ዛሬ እየሆነ ስላለው አትናገሩም? ለምን ህዝብ እያስለቀሰ ስላለው የአመራር ችግር በተለይም አመራሩ ከላይ እስከታች የተዘፈቀበትን ሌብነትና ዘረፋ እንዲሁም የአስተዳደር ችግር አንነጋገርም?” የሚል ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ ከመካከላቸው “አሸባሪ” እየተባሉ ለአንድ ሰው እስከ 15 ታጣቂዎች እየተላኩ በግፍ የሚካሄደውን እስር ለአብነት በማንሳት ሞግተዋል።
አንድ ሰራተኛ “ መንግስቱ ሃይለማርያም እንደዛሬ ባለስልጣኖች ለራሱ ለራሱ ቤት አልሰራም፣ ለህዝብ ቤት ሰራ እንጂ የህዝብ ቤት እያፈረሰ አላፈናቀለም፣ ለጎዳና ተዳዳሪነት አልዳረገም፡፡ ስለዚህ የሌሉትን መልስ የማይሰጡትን በመውቀስ የዛሬዎችን ሌቦችና ዘራፊዎች በሙስና የተዘፈቁትን ለመሸፈን መሞከር ጥልቅ ተሃድሶ ሊሆን አይችልም፣ ከቻላችሁ ለምንጠይቀው መልስ ስጡን ፣ካልቻላችሁ ጥቄዎቻችን መልስ ለመስጠት ለሚችሉ አቅርቡልን ›› ብሎአል።
ሌላ ሰራተኛ ደግሞ “እኛ መሬት አልሸጥንም፣ ቤት አላፈረስንም፣ በብዙ መቶ ሺ ብሮች የሚገነባ ቪላ ቤት አልሰራንም ፣ ችግሩ ያለው እዚያው እናንተ ዘንድ ሆኖ በኑሮ ውድነት እየተሰቃዬን ያለነውን ምን አድርጉ ነው የምትሉን ? የእኛ ነገር ‹‹ምንም ቢታለብ በገሌ›› እንዳለችው እንስሳ ነውና እባካችሁ የሙስናው ‹ ዝሆንና አንበሳው › ከላይ እስከዞን ተቀምጦ ባለበት ትንኝን በተሃድሶ ሥም ማዋከብ ምንም ለውጥ አያመጣምና ተዉን ኑሮኣችንን እናስታምበት›› ብለዋል፡፡
አንድ የጤና መምሪያ የሰው ሃብት ልማት ሠራተኛ ‹‹ ከዚህ በፊት አሁን ያነሳችሁትን አጀንዳ በተለይም በአመራሩ ላይ የሚታየውን ችግር በተመሳሳይ የውይይት መድረክ በማንሳታችን ከመድረክ ደግሜ የማልናገረው የግል ስብዕናን የሚነካ መልስ ሲሰጠን ነበር፡፡ ዛሬስ ይህ መድረክ ከዚያ የተለየና ከማዕከልና የክልል መንግስት እንደምንሰማው ዓይነት በባለሥልጣናት ላይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ነው ወይስ እንደተለመደው ሠራተኛውን ለማሸማቀቅ ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሰራተኞች ላነሱዋቸው ጠንካራ ጥያቄዎች ከመድረክ አሳማኝ መልስ መስጠት አልተቻለም። መድረክ መሪዎቹ ተከታታይ የግምገማ መድረኮች ስለሚኖሩ ያን ጊዜ ይነሳል በማለት ጥያቄዎችን አድበስብሰው አልፈውታል።
የጋራ ውይይት መድረክየካቲት 01/09 ከሰዓት በፊት ያለምንም የሚጨበጥ ውጤት አብቅቶ ከሰዓት በኋላ ሠራተኛው ‹‹ በየሴክተር መ/ቤቱ ተከፋፍሎ ወደ ግምገማ እንደገባ ፣ ግምገማው ዓርብ የካቲት 3 ቀን 2009 ዓም እንደሚጠናቀቅ በስብሰባው የሚሳተፉ ምንጮች ገልጸዋል።
በኦሮምያ እና በአማራ ክልሎች የተካሄዱ የመንግስት ሰራተኞች ስብሰባ በተቃውሞ መጠናቀቃቸውንና ገዢው ፓርቲ ሰራተኛውን በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞም ይሁን በአገሪቱ ለሚታየው ችግር ተጠያቂ ለማድረግ እና ራሱን ከተጠያቂነት ለማውጣት ያቀደው እቅድ በሰራተኞች ብርታት መክሸፉን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።