እስክንድር ነጋም ሆነ አንዱአለም አራጌ አሸባሪዎች ሳይሆኑ የይስሙላ ፍርድ ቤት ሰለባዎች ናቸው ሲሉ ኬት ባርት የተባሉ የመብት ተሟጋች ገለጹ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 11/2009) በሽብር ወንጀል የተከሰሱትና የተፈረደባቸው እስክንድር ነጋም ሆነ አንዱአለም አራጌ አሸባሪዎች ሳይሆኑ የይስሙላ ፍርድ ቤት ሰለባዎች ናቸው ሲሉ ኬት ባርት የተባሉ የመብት ተሟጋች ገለጹ።

ፍሪደም ናው የተባለው ተቋም የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ኬት ባርት መሰረታዊ የሰው ልጆች መብቶችን ወንጀል እንዲያደርግ በተቃኘው ህግ ዜጎች ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መቀመጫውን በዩኤስ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የመብት ተሟጋቹ ፍሪደም ናው የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ኬት ባርት በተለይ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ነጻ አይደሉም ተብለው የሚጠቀሱ ብቻ ሳይሆን በግልጽ ያለ አንዳች ማስረጃ ውሳኔ የሚያሳልፉ ጉዳይ አስፈጻሚ ተቋማት ናቸው ብለዋል።

የፍሪደም ናው የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር እንዲሁም የእስክንድርና አንዱአለም መብት አቀንቃኝ በመሆን የሚንቀሳቀሱት ኬት ባርት የጸረ ሽብር ህግ ተብሎ እየተሰራበት ያለው መመሪያ በግልጽ ቋንቋ የመብት ተሟጋቾችን ዝም ለማሰኘት የተዘጋጀ እንደሆነም አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ቀልድ ነው ሲሉም ገልጸውታል።

አለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም መብትና ነጻነትን ለማክበር ቃል የገባው የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን መብቶች የጠየቁትን እያሰረ በአሸባሪነት ሽፋን ሊሻገር እየሞከረ እንደሆነም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የመብት ተሟጋቾችን ለማፈን የጸረ ሽብር ህጉ ስራ ላይ መዋሉ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ በቂ ግንዛቤ እያገኘ መምጣቱንም ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግስታት ከአምስት አህጉራት በተውጣጣ ቡድን የእስክንድርን ጉዳይ ለአብነት ወስዶ ባደረገው ጥናት እስክንድር በግፍ መታሰሩንና መብቱ መገፈፉን አረጋግጧል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ሰዎችን የሚከታተለው ቡድን ይህን አቋሙን ይፋ ያደረገው በ2013 መሆኑም ተመልክቷል።

አሜሪካዊቷ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች ኬት ባርት በየትኛውም አለም በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የእነ አንዱአለም ጉዳይ ቢቀርብ በአንዳቸውም አሸባሪ ተብለው ሊጠቀሱ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግስት ለዚህ ጨቋኝ ስርአት የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲመረምርም ጠይቀዋል።

ለጸጥታ ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት የሰብአዊ መብትን ችላ ማለት የተሳሳተ ስሌት ነው።ስለዚህ ይህ ስህተት እንዲታረም ሊነገር ይገባል ሲሉም ለአሜሪካ መንግስት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።