ኤች አር 128 እንዲጸድቅ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይዘናጉ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 19/2010) በአሜሪካን ኮንግረስ ለውሳኔ የቀረበው ኤች አር 128 እንዲጸድቅ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይዘናጉ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።

በአውሮፓና በሌሎች ክፍለ አለማት የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እየሰጡ መሆኑም ታውቋል።

በቀጣይም በመላው አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በግፍ ለታሰሩት ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ተከራካሪ በመሆን በያሉባቸው ግዛቶች ለሚገኙ የምክር ቤት አባላት ቢሮአቸው በመገኘት፣በደብዳቤና በስልክ መልዕክታቸውን እንዲያደርሱ ጥሪ ቀርቧል።

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚንቀሳቀሰው ማህበረ ኢትዮጵያ ለነጻነትና ለፍትህ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጣሰው መላከሕይወት ለኢሳት በሰጡት አስተያየት የማህበራቸው አባላት ህጉ እንዲጸድቅ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በመስከረም 8 /2010 በአሜሪካን ምክር ቤት ካፒቶል ሒል የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ከዲሲ ግብረሃይልና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ማሳካታቸውን አቶ ጣሰው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአሜሪካን የተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካባቢያቸው ለተመረጡ ሴናተሮች፣ኮንግረስ አባላትና የግዛቱ ምክር ቤት አመራሮች በአካልና ስልክ በመደወል መልእክቱ እንዲደርሳቸው የዘመቻ ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የማህበራቸው አባላትና ደጋፊዎቻቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ሁኔታ የሚመልከተውን ረቂቅ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው በቦታው በመገኘት ግፊት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የውሳኔ ቀኑ ተሰርዟል እየተባለ በሚወራው ወሬ ሳይዘናጋ ዘመቻውን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ማህበረ ኢትዮጵያ ለነጻነትና ፍትህ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ኤች አር 128 የውሳኔ ሀሳብ በአሜሪካን የተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ከፍተኛ ዘመቻ ከሚያደርጉት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆኑትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ጋሻው ገብሬ ናቸው።

አቶ ጋሻው የውሳኔ ሀሳቡ ለምክር ቤት እስከመቅረብ መድረሱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጥረታቸው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ወደፊትም በሀገራቸው እጣ ፋንታ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያመላክት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አክለው ገልጸዋል።

በአውሮፓና በሌሎች ክፍለ አለማት የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እየሰጡ መሆኑም እንዳስደሰታቸው አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

በቀጣይም በመላው አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በግፍ ለታሰሩት የሀገራችን ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ተከራካሪ በመሆን በያሉባቸው ግዛቶች ለሚገኙ የምክር ቤት አባላት ቢሮአቸው በመገኘት፣በደብዳቤና በስልክ መልዕክታቸውን እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።