ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት ብቻ 12.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ አለባት

ግንቦት ፯ ( አባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያ ከቻይና ባንኮች ብቻ እኤአ ከ2000-2014 ከፍተኛ ብድር ከወሰዱ አምስት የአፍሪካ አገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ የቻይና አፍሪካ ጥናት ማእከል አስታወቋል።
ጥናቱ በተጠቀሱት ዓመታት ብቻ አንጎላ 21 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ስትወስድ፣ ኢትዮጵያ በ12 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ ብድር ወሳጅ አገር ተብላለች። ሱዳን በ 5 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ፣ ኬኒያ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ወስደዋል።
አንጎላ፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የመሳሰሉ አገራት ስለብድሩ በግልጽ ስለማያወሩ፣ ብድሩ ስለአመጣው ጥቅምና ጉዳት መናገር እንደማይቻል ጥናቱ አመልክቷል። የእዳ ጫናውን አስመልክቶ ሂዋንግ ሲናገሩ ”የብድር ስምምነነቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም። የብድሩ አስፈላጊነት ጨምሮ በምን ላይ እንደሚውል እንዲሁም በአገራቱ ላይ ብድሩ ስለ ሚያስከትለው አሉታዊ ጫና በግልጽ አይታወቅም” ማለታቸውን አፍሪካንስ ቢዝነስ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ እኤአ ከ2014 እስከ 2017 ምን ያክል ገንዘብ ከቻይና እንደተበደረች አልተገለጸም። ከቻይና የተወሰዱት ብድሮች አብዛኞቹ በ10 አመት እድሜ ውስጥ የሚከፈሉ ናቸው።
አትዮጵያ ከሌሎች አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ ከግል ባንኮችና ከምእራባውያን መንግስታት ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ በብድር መልክ ወስዳለች። አገሪቱ ከአለማቀፍ መንግስታት እና አገራት የተበደረችውን የገንዘብ መጠን እስካሁን በትክክል ይፋ አላዳረገችም።