ኢትዮጵያ ተመድ የእርዳታ ምግብ አቅርቦት በተያዘው ወር ሊያልቅ ይችላል ሲል የሰጠውን ማሳሰቢያ አስተባበለች

ኢሳት (ሰኔ 5 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሃገሪቱ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የተጋለጡ ወደ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች የሚያስፈልጋቸው የምግብ አቅርቦት በተያዘው ወር ሊያልቅ ይችላል ሲል የሰጠውን ማሳሰቢያ አስተባበለች።

አለም አቀፍ ተቋማትና የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም ተረጂዎች ከሰኔ ወር መገባደጃ ጀምሮ የሚቀርብላቸው የምግብ ድጋፍ እንደማይኖር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን የሰጡ የመንግስት ባለስልጣናት በችግሩ ምክንያት 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ጉዳት እንደሚደርስባቸው መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። 

የአደጋ መከላከል አስተዳደር ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ ለተረጂዎች የሚሆን የምግብ አቅርቦት ለሁሉም ተረጂዎች ያልቃል መባሉ ትክክለኛ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

ይሁንና በተወሰኑ አካባቢዎች ለተረጂዎች የሚቀርብ የምግብ አቅርቦት እንደማይኖርና 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ለችግር እንደሚጋለጡ አቶ ምትኩ ለዜና አውታሩ ገልጸዋል። የተፈጠረውን የምግብ አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍን እንዲያደርግለት ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ለጋሽ አካላት የሚጠበቀውን ድጋፍ በአፋጣኝ የማያቀርቡ ከሆነ መንግስት ከልማት በጀት ገንዘብን በመውሰድ ለተረጂዎች ዕርዳታን እንደሚሰጥ ሃላፊው አክለው ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት ላቀረበው የምግብ ድጋፍ ጥሪ በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት ድርቁ እየተባባሰ መምጣቱን ሲገልፅ ቆይቷል። በተለይ በሶማሌ ክልል ጉዳት እያደረሰ ያለው የድርቁ አደጋ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

በተለይ በተያዘው ወር መጨረሻ 7.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተረጂዎች የሚቀርብ የምግብ ድጋፍ ሊያልቅ ይችላል መባሉ ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል ተብሎ ስጋት መኖሩን የአለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WPF) በማሳሰብ ላይ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመቅረፍ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ቢገልፅም፣ እስካሁን ድረስ ሊገኝ የቻለው ድጋፍ ከግማሽ በታች መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የአለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ የሆኑት ጆን አይሊፍ “ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ችግር ውስጥ ትገኛለች” ሲሉ ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።

ተወካዩ ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ የምግብ ድጋፍ አቅርቦቱ  መስተጓጎል እንደሚያጋጥመው አክለው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ጆን ግራም ተረጂዎች የሚያስፈልጋቸው የምግብ አቅርቦት በሰኔ ወር ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተመሳሳይ ስጋት መግለጻቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

“ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ከወዲህ መገመት ይቸግረናል” ሲሉ ተወካዩ ገልጸዋል።