ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ዝውውር ላይ አፈና መፈጸሟን የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አስታወቀ

ታኅሣሥ  ፭ (አምስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ  አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ተከትሎ  በሕገወጥ መንገድ ድረገጾችን እና የኢንተርኔት አገልግሎትን በተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም መዝጋቱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።

ሕዝባዊ ተቃውሞው ከተነሳበት እ.ኤ.አ. ኖቨምበር 2015 ጀምሮ ማኅበራዊ ድረገጾችን፣ የግል የዜና አውታር ድረገጾችን በመዝጋት ሕገወጥ የሆነ የመብት ጥሰቶች መፈጸሙን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። አስቸኳይ የጊዜ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሃይል እርምጃዎችን ይጠቀማሉ። አንዳንዴም ገዳዮችን በማሰማራት በንፁሃን ዜጎች ላይ አካላዊ ጉዳቶችን ጨምሮ ግድያን ይፈፅማሉ። አደገኛ የሆኑ የተለያዩ አፋኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች በመጣስ የመረጃ እና መገናኛ አውታሮች እንዲገደቡም ያደርጋሉ። በአብዛሃኛው የአገሪቱ ክፍሎች የኢንተርኔት መስመሮችን በመዝጋት፣ የኢንተርኔት መስመሮች ደካማ እንዲሆኑ በማድረግ እና ማኅበራዊ ድረገጾችና  ሚዲያዎች እንዲታፈኑ በማድረግ የመረጃ ዝውውሩን ለመቆጣጠር ሙከራ መደረጉን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ አመላክቷል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኔት ወርክ ጥናት ቡድን Open Observatory of Network Interference (OONI)  ከሰኔ እስከ ሕዳር ወር እ.ኤ.አ. 2016 ድረስ ባጠናው ሪፖርት ዋትስ አፕን  ጨምሮ የመገናኛ አገልግሎቶች ዝግ መሆናቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አፈናን ለመፈጸም እንዲያስችለው Deep Packet Inspection (DPI) ጨምሮ  ዘመናዊ አፋኝ የቴክሎሎጂ ግብአቶችን ይጠቀማል። ”ገዥው መንግስት የኢንተርኔት አፈናን በማጠናከር የፖለቲካ ምኅዳሩን ማጥበቡን፣  የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በነፃነት የመደራጀት እንዲሁም  ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን ማፈኑን አረጋግጠናል ሲሉ የ OONI ዳይሬክተር ተናግረዋል””

እንዲሁም  የኢንተርኔ አገልግሎት በመደበኛ ደረጃ ለተጠቃሚው እንዳይዳረሱ የተለያዩ የማፈኛ ስልታዊ መንገዶችን በመጠቀም ተደራሽነታቸውን ማስተጓጎል የኢትዮጵያ መንግስት ዓይነተኛ ምግባር መሆኑን ደርሰንበታል” ሲሉ ዳይሬክተሯ  ወ/ሮ ማሪያ ዜኖ አክለው አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃሳብ እንዳይሰማ፣ ነጻ መገናና ብዙሃን እንዳይኖር አፈናው እያደር ተጠናክሮ መቀጠሉን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በልዩ ሪፖርቱ ዘግቧል።