ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ከሌለባቸው ከመጨረሻዎቹ ሃገራት ተርታ መመደቧ ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ከሌለባቸው የመጨረሻዎቹ አምስት ሃገራት ተርታ እንደምትመደብ ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ የተባለ አለም አቀፍ ተቋም ገለጸ።

ተቋሙ የ2017 ጥናታዊ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ እንደገለጸው ኢትዮጵያ ከ161 ሃገሮች ጋር ስትነጻጸር የሰላምና መረጋጋት እጦትን በተመለከተ 134 ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ ሰላሟን እያጣቸው የመጣችው በሃገሪቱ የተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ነው። በሃገሪቱ በከፊል በብሄር ላይ የተመሰረ ውጥረት መኖሩን ጥናቱ ያመለክታል።

በዚህ ቀውስና ውጥረትም ሳቢያ በኢትዮጵያ ካልፈው መስከረም መጨረሻ ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ እንደሚገኝ ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ በጥናቱ ገልጿል። ይህም በሃገሪቱ ያለው ሰላም አስተማማኝ አለመሆኑን ያመለክታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ብዙ ገደቦች እንዲጥልና ወታደራዊ ሃይሉንም እንደፈለገ እንዲጠቀም አስችሏል ሲል ጥናቱ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የሰላም ዕጦት መባባሱንና የኢትዮጵያን ደረጃ ዝቅ ማድረጉን ጥናቱ አመልክቷል። በሃገሪቱ ያለው የሰላምና የመረጋጋት እጦት ወታደራዊ ወጪዎቿ እንዲጨምር ማድረጉም ተገልጿል። ምንም እንኳን የአለም የሰላም ሁኔታ የዘንድሮውን ካለፈው አመት የተሻለ ቢሆንም፣ ባለፉት 10 አመታት በጥቅሉ ሲታይ ግን ምድራችን የጸጥታዋ ሁኔታ በእጅጉ የተረበሸ መሆኑንም ጥናቱ አሳይቷል።

በተቋሙ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ከ161 ሃገሮች ጋር ስትነጻጸር የሰላምና መረጋጋት እጦቷ በ134ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ እንዳለው ሁከትና አለመረጋጋት የአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት ፍጆታ ወይም ጂዲፒ 12.6 በመቶው የሚሆነውን ዋጋ ያሳጣል። ይህም በቀን 5.4 ዶላር ማለት ነው። እናም ለሰላም ግንባታ አንድ ዶላር ወጪ ቢደረግ በግጭት ምክንያት ሊታጣ የሚችልን 16 ዶላር ሊያስቀር እንደሚችልም ጥናቱ አመልክቷል።