ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ በቂ ቡና ማቅረብ እንዳልቻለች ተገለፀ

ጥር 22 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የቡና ላኪዎች ባለባቸዉ የዉስጥ ችግር ምክንያት መንግሰት በዘንድሮዉ አመት ከያዘዉ 270ሺህ ቶን አመታዊ እቅድ ዉስጥ 25 በመቶ ያህሉን እንኳ እስካለፈዉ 2ኛዉ ሩብ አመት መጨረሻ ድረስ ለዉጭ ገበያ ማቅረብ እንዳልቻለ አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘገበ።

ይኸዉ ሁኔታ ያስደነገጣቸዉ የንግድ ሚኒስትሩ ከበደ ካሳና በሚኒስትር ማእረግ ያሉት ያእቆብ ያላ ባለፈዉ ሳምንት ዉስጥ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር መሪዎች ጋር አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል።

በስብሰባዉ ላይ የኢትዮጵያ የሸቀጥ ልዉዉጥ  ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን፤ ሁለት የኢትዮጵያ የሸቀጦች ባለስልጣን ምክትል ዲሬክተሮች፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ተወካይ፡ እንዲሁም የኦሮሚያና የደቡብ ህዝቦች ክልሎች የንግድ ቢሮ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በቡና አቅራቢዎችና በቡና ላኪዎች መካከል የሚኖረዉ ግንኙነት የዉጭ ገበያዉን ሂደት እንዲያቀለዉ የተጠራዉ ስብሰባ የተበተነዉ ያለ እልባት አንደሆነ አዲስ ፎርቹን ገልጿል።

በስብሰባዉ ወቅት በመንግሰት ሃላፊዎችና በቡናዉ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወካዮች መካከል የሞቀ ከፍተኛ ክርክር የተካሄደ ቢሆንም በዉጭ ገበያዉ ላይ ለደረሰዉ ዉድቀት እዉነተኛዉ ምክንያት ለማወቅ አልተቻለም።

ባለፈዉ አመት በንግድ ሚኒስቴር ትእዛዝ ከሁለት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ ከ500 ቶን በላይ የዉጭ ኮንትራት ሳይፈፅሙ በመጋዘን ቡና አስቀምጠዋል በማለት መንግሰት የወነጀላቸዉና ከኢትዮጵያ የሸቀጥ ልዉዉጥ ቡና እንዳይገዙ የተከለከሉ 41 ቡና ላኪዎች ፣ እንዲሁም ከ3 እስከ 6 ወር ከንግድ ስራቸዉ የታገዱ 51 ቡና ላኪዎች ይገኛሉ።

ከዚህ ሌላ  አስፈላጊ ነገሮች ባልተሟሉበት  እስከ ጅቡቲ እና ገዢዎች እስከሚገኙባቸዉ አገሮች ወደብ ድረስ ቡና በኮንቴነር እንዲላክ ባለማወቅም ሆነ በግትርነት በንግድ ሚኒስቴር የተሰጠዉ ዉሳኔ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ የቡና አይነት ዝርያ ባላት አገር ላይ ሊሰራ የማይችል በመሆኑ ለስራዉ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በኒዉ ዮርክ አለምአቀፍ ገበያ ላይ ያለዉ የቡና መሸጫ ዋጋ በኪሎ 2 ዶላር ከ20 ሳንቲም መሆኑ እየታወቀ የቡና ላኪዎቹ ከኢትዮጵያ የሸቀጥ ልዉዉጥ ቡናዉን በጨረታ እንዲገዙ የሚገደዱት 2 ዶላር ከ40 ሳንቲም በላይ መሆኑ ለማሽቆልቆሉ ሌላው ምክንያት ነው።

አገሪቱ ከዉጭ ንግድ ለማግኘት ካቀደችዉ 4 ቢሊዮን ዶላር ዉስጥ ቡና 30 በመቶዉን የሚሸፍን በመሆኑ አሁን የተፈጠረዉ ችግር ጉዳት ሊያሰከትል እንደሚችል አዲስ ፎርቹን ገልጿል።

የህወሀት ኩባንያ የሆነው ጉና የንግድ ድርጅት ወደ ቡና መላክ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ተቀናቃኞችን የግል ነጋዴዎች ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ እንደሚሞክሩ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።