ኢትዮጵያውያን የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ በደረሰው የመኪና አደጋ ሶስት ልጆቻቸው ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 12/2009)ከአሜሪካ ወደ ካናዳ አልበርታ አምርተው በጉብኝት ላይ በነበሩ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ በደረሰው የመኪና አደጋ ሶስት ልጆቻቸው ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተሰማ።

በአደጋው ከባድ የመቁስል አደጋ የደረሰባቸው የልጆቹ አባትና እናት ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን አንድ ሕጻንን ጭምሮ 3ቱ ልጆቻቸው ግን አደጋው በደረሰበት ስፍራ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ከአሜሪካ ወደ ካናዳ አልበርታ አምርተው በጉብኝት ላይ በነበሩ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ በደረሰው የመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጡት አንዲት የ16 አመት ታዳጊ ሴት፡የ11 አመት ወንድና የ10 ወር እድሜ ያላት ህጻን መሆናቸውን ግሎባል ኒውስ ዘግቧል።

አደጋው የደረሰው ባለፈው ረቡእ አንድ ከባድ የጭነት መኪና በከፍተኛ የመተለለፊያ መንገድ ላይ የአንድ ቤተሰብ አባላት የነበሩትን ኤስዩቪ መኪና በመግጨቱ ነው ተብሏል።

ግጭቱ የደረሰው በምስራቅ ማእከላዊ አልበርታ ሐና አልታ በተባለ ስፍራ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።
ይህም 570ና 36 ተብለው በሚታወቁ ከፍተኛ የመተላለፊያ መንገድ መጋጠሚያ ላይ መሆኑም ታውቋል።

የልጆቹ እናትና አባት ክፉኛ ቆስለው ፍትሒልስ በተባለ የሕክምና ተቋም እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ሁለቱም አደጋው ከደረሰበት ስፍራ በሔሊኮፕተር ተወስደው ሕክምና ላይ በመሆናቸውንና በሰመመን መስጫ ክፍል በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው ግለሰብም መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት መትረፉን የካናዳ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።