ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ እንዲወጡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ 4 ቀን ቀረው     

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 13/2009) የሳውዲ አረቢያ መንግስት በሃገሩ ይኖራሉ ያላቸውን 5 ሚሊየን ህገ ወጥ ስደተኞችን ለማስወጣት እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 29/2017 ነበር የሶስት ወራት የጊዜ ገደብ ያስቀመጠው።

እንደአውሮፓውያኑ ሰኔ 25/2017 ደግሞ የጊዜ ገደቡ ለተጨማሪ አንድ ወር መራዘሙን ይፋ ማድረጉ ይታውሳል።

በሳውዲአረቢያ መንግስታዊ ተቋማት መረጃ መሰረት በሳውዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩት በአጠቃላይ ቁጥራቸው 5 ሚሊየን የሚጠጋ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያውያኑ ብዛት 400ሺ እንደሆነም ተመልክቷል።

በመጋቢት ወር የወጣውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎም ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት ኢትዮጵያውያን ብዛት 60ሺ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

130 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የመውጫ ቪዛ ተቀብለው ለመመለስ ዝግጅት ማጣናቀቃቸው ታውቋል።–ይሁን እንጂ ስለ ቀሪዎቹ 210ሺ ኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

በሳውዲ አረቢያ መንግስት ማስጠንቀቂያ መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሀገሪቱን የማይለቁ እስራት እንዲሁም ከ4 ሺህ እስከ 27 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

የጣት አሻራቸውን እንዲሰጡ የሚገደዱ ሲሆን በዚህም ተመልሰው ሳውዲአረቢያን እንዳይረግጡ ክልከላ እንደሚጣልባቸው ተመልክቷል።