ኢትዮጵያውያን አይሁዶች አላግባብ እየተጨቆኑ መሆኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 25/2009)የእስራኤል ጺዮናውያን እያራመዱት ባሉት ዘረኝነት በኢትዮጵያውያን አይሁዶች ላይ የከፋ ሰቆቃ ማሳደሩን አንድ ዘገባ አመለከተ።
አህሉልባይት የተባለው የዜና ወኪል እንዳወጣው ሪፖርት ከሆነ ጺዮናውያኑ የኢትዮጵያውያኑን ጉልበት አላግባብ እየበዘበዙ መሆኑን ያመለክታል።
ዘረኝነትን እያራመዱ ያሉት ጺዮናውያን በሀገሪቱ ቁልፍና ከፍተኛ የሚባሉ ቦታዎችን የያዙና የሚኖሩትም የቅንጦት በሚባሉ ዘመናዊ ቤቶች ነው።
በዘመናዊ ቤቶቻቸው ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን የሚያሰሩት እንደጥንቱ የባሮች ስርአት ነው ይላል ዘገባው።
የእስራኤል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣው ሌላ አስገራሚ መረጃንም ዘገባው ያነሳል።
ከአራት አመት በፊት አንዲት የኢትዮጵያውያን አይሁዶች ተወካይ ደም ለመለገስ ብትፈልግም ጺዮናውያኑ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። ለዚህ ያስቀመጡት ምክንያት ደግሞ የትውልደ ኢትዮጵያንን ደም አንፈልግም የሚል ነው።
ከብዙ ውዝግብ በኋላም ደሟ እንዲወሰድ ቢደረግም ማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲቀመጥ ተደረገ እንጂ አገልግሎት ላይ እንዲውል አልተፈቀደም።
ዘገባው የጺዮናውያኑን የከፋ ዘረኝነት ሲገልጽም ለኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳይሆን በነሱ እምነት ውስጥ ላሉ እስራኤላውያንም አይመለሱም ብሏል።
ዘገባው ሲያጠቃልልም በኢትዮጵያውያን አይሁዶች ላይ እያደረሱት ያለው ጭካኔ ግን የጥንቱን የባሮች አገዛዝ ስርአት ያስታውሳል ነው ያለው።