ኢትዮጵያዊያን ቤተ እስራኤላዊያን በደረሰባቸዉ የዘር መድልዎ ያነሱት ተቃዉሞ እንደሚጣራ ፖሊስ አረጋገጠ

ጥር 4 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-በእየሩሳሌም ኪሪያት ማላኪ በተባለዉ አካባቢ ነዋሪዎች ቤታቸዉን ለኢትዮጵያዊያን ቤተ እስራኤላዊያን ላለማከራየትና ላለመሸጥ በፊርማ ያደረጉት ስምምነት ያስቆጣቸዉ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላቀረቡት አቤቱታና ተቃዉሞ የተሰጣቸዉ መልስ ሌላ ቁጣን አስከትሏል።

የቤተ እስራኤላዉያኑን አቤቱታ ለመስማት የተገኙት የእስራኤል የስደተኛ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ ሶፋ ላንድቨር “ ከኢትዮጵያ የመጡት ፈላሻዎች የእስራኤል መንግሰት ላደረገላቸዉ ዉለታ ምስጋና ሊያቀርቡ ይገባል” በማለት የሰጡት ምላሽ  “በዘር ላይ የተመሰረተ ዘለፋ “ መሆኑ በኢትዮጵያዉያኑ ቤተ እስራኤላዉያን ዘንድ ይበልጥ ቁጣን ቀስቅሷል። 

“ ከ2010 ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለኢትዮጵያዉያኑ ተመድቦ የኢትዮጵያ ስደተኞች ያሉባቸዉን ጉዳዮች ለመፍታት፤ በተለይም የስራ ቅጥርን በተመለከተ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ብዙ ስራ ሰርቷል። ከሌላዉ የእስራኤል ህብረተሰብ በተለየ ደረጃ ኢትዮጵያዉያን ቤተአስራኤላዉያን በዕድገትና በአጠቃላይ ከሕዝቡ ጋር ባላቸዉ ትስስር በብዙ አመታት ወደ ሁዋላ የቀሩ ናቸዉ። ልዩነቱ የሰፋ ቢሆንም የእስራኤል መንግሰት ስደተኞቹን ለመቀበል የተቻዉን ሁሉ አድርጓል።” በማለት ሚኒስትሯ የሰጡት ምላሽ ቤተ እስራኤላዊ ኢትዮጵያዉያንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም አስቆጥቷል።

“አንዳቸሁ ከሌላችሁ ትበልጣላችሁ በማለት በዜጎች መካከል ልዩነት ለመፍጠር ይህ መንግስት የሚናገረዉ መቆም አለበት፤ ዜጎች መብትና ክብራቸዉ ሊጠበቅ ይገባል። መንግስት ለዜጎቹ የሚያደርገዉ ነገር እንደዉለታ ሊቆጠርለት ወይንም ሊመሰገንበት አይገባም። ”  በማለት የሰራተኛዉ ፓርቲና የአንድ ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሚኒስትሯን ተችተዋል።  

“ኢትዮጵያዉያኑ ስደተኞች የዚህ አገር ኩሩ ዜጎች በመሆናቸዉ መብታቸዉ ሊጠበቅ ይገባዋል፤ በመንግስት የሚደረግላቸዉ ሁሉ መብታቸዉ በመሆኑ ነዉ።” በማለት ጠ/ሚኒስትር ቢንያሚን ናትኒያሁ ከመናገራቸዉም በላይ፣  በኢትዮጵያ ጉዳይ አማካሪያቸዉ የሆኑት አላሊ አድማሱ ይህንን በኢትዮጵያዉያን ላይ የተፈጠረ የዘረኝነት ክስተት ለማስወገድ እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥተዋል።

የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሺሞን ፔሬዝ በበኩላቸዉ ባደረጉት ንግግር “ ሁላችንንም የሚያሳፍር ነገር ነዉ። በእስራኤል ዉስጥ የምንገኝ ሁሉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ልናመሰግናቸዉ ይገባል፡ እነሱ ሳይሆኑ እኛን ማመስገን ያለባቸዉ። በህብረተሰብ መካከል ልዩነት የሚፈጥሩ በሚፈፅሙት ተግባርና በሚናገሩት ሊያፍሩ ይገባቸዋል” ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያዉያኑ ቤታቸዉን ላለማከራየትና ላለመሸጥ የኪርያት ማላኪ አካባቢ የቤት ባለቤቶች በዘረኝነት የወሰዱት እርምጃ በፖሊስ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መግለጻቸዉን ጀሩሳሌም ኒዉስ አስታዉቋል።