ኢትዮጵያዊው የታክሲ ሾፌር ሩብ ሚሊዮን ዶላር ረስቶ ለወረደው ተሳፋሪ ገንዘቡን መለሰ

መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በላስ ቬጋስ የታክሲ ሾፈር የሆነው አዳም ወልደማርያም፣ አንድ በቁማር 250 ሺ ዶላር አሸንፎ ገንዘቡን ታክሲው ውስጥ ረስቶ ለወረደ ሰው ነው ገንዘቡን የመለሰው።

አዳም ወልደማርያም  በላፕቶፕ መያዢያ ውስጥ ታጭቆ ያገኘውን ገንዘብ እንዳተመለከተ ወዲያውኑ ለተቆጣጠሪው ማስረከቡን የደይሊ ሜል ሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።

ተሳፋሪው ገንዘቡን መልሶ በማግኘቱ መደሰቱንና ለወልደማርያምም 2 ሺ ዶላር እንደሰጠው ታውቋል።

አዳም ገንዘቡን እንዳገኘ ታኪሲውን ቀደም ብሎ ሲያሽከረክር ለነበረው ኢትዮጵያዊው ጉደኛው ገንዘቡ የእርሱ እንደሆነ እንደጠየቀውና ጓደኛውም የእርሱ አለመሆኑን ገልጸለታል።

ሁለቱም ገንዘቡን ለጸጥታ አስከባሪዎች ማስረከባቸውን  በአንድ ሰአት ውስጥም በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝ ወጣት በቁማር ያሸነፈውን ገንዘብ ታክሲ ውስጥ ጥሎ መውረዱን ለጸጥታ አስከባሪዎች አስቀድሞ በማሳወቁ  ገንዘቡን ተረክቧል።

የአዳም ጓደኛ የሆነው አሌክስ ብርሀኑ  በሰጠው አስተያየት ግለሰቡ የሰጠው ገንዘብ ትንሽ መሆኑ ቢያሳዝነውም ፣ ተሳፋሪዎች በውጭ አገር አሽከርካሪዎች ላይ  ያላቸውን አመለካከት ሊቀይር እንደሚችል ያለውን እምነት ለላስቬጋስ ሪቪው ተናግሯል።

አዳም በታማኝነቱ ጀግና ተብሎ መወደሱን ዘገባው ያመለክታል።