ኢብሳ አስፋው አቶ ናትናኤል መኮንንን ለመደብደብ ያደረገው ሙከራ በ እስረኞች ትብብር ከሸፈ

ሚያዚያ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በግድያ ወንጀል 25 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው  ይባስ አስፋው፤ ሆነ ተብሎ ገና ካልተፈረደባቸው እስረኞች ጋር እንዲቀላቀል ከተደረገ በሁዋላ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር  አቶ አንዷለም አራጌን በአሰቃቂ ሁኔታ በመደብደብ   ከፍ ያለ የአካል ጉዳት እንዳደረሰባቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ይባስ አስፋው፤ በአቶ አንዷለም ላይ  ጉዳት በማድረሱ ከተለያየ አቅጣጫ  ከፍ ያለ ተቃውሞ እየተሰማ ባለበት ወቅት  የእስር ቤቱ ሀላፊዎች  ይባስን ከነ አንዷለም ክፍል አስወጥተው ሌለኛው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ናትናኤል መኮንን ወደታሰሩበት ክፍል በማዛወር  ከአጠገባቸው በሚገኝ ቦታ ላይ እንደመደቡት ይታወቃል።

ሰሞኑን   ይባስ አስፋው ከጎኑ የሚገኙትን የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት አባል አቶ ናትናኤል መኮንንን ለመደብደብ ያደረገው ሙከራ ፤በክፍሉ ውስጥ በሚገኙ እስረኞች ትብብር መክሸፉን የዜና ፍኖተ-ነፃነት የእስር ቤት ምንጮቹን በመጥቀስ ዘግቧል፡፡

የዜናው ምንጮች፦” “በቅርቡ ከሌላ ክፍል ተዛውሮ ወደ እነ ናትናኤል ክፍል የመጣው  ይባስ አስፋው፤ ከአቶ ናትናኤል ጐን እንዲተኛ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ምክንያት እየፈለገ የትንኮሳ ሥራ ሢሰራ ቆይቷል፡፡” ይላሉ፡፡

አቶ ናትናኤል በሚተኙበት አካባቢ የምግብ ፍርፋሪ መጣል፣ አክታ መትፋት፣ሲወጡና ሲገቡ ያልተገቡ ፀያፍ ተግባራትን መፈፀም   የይባስ መደበኛ ሥራው ሆኖ መክረሙን  ምንጮቹ ተናግረዋል።

ይባስ ይህን ሁሉ እየፈፀመ  የአንድነቱ አመራር ዝም ቢሉትም ፤ይባስ ብሎ ሰሞኑን በቀጥታ አቶ ናትናኤልን ለመደብደብ ሙከራ ማድረጉን የገለፁት ምንጮቹ፤ ይሁንና በክፍሉ ውስጥ ያሉ እስረኞች ፦“እስቲ ጫፉን ትነካዋለህ! ?”በማለት በጋራ በመነሳታቸው የድብደባው እቅድ ከሽፏል”ብለዋል፡፡

በመቀጠልም “ አቶ ናትናኤል ወደ ጥበቃ ሠራተኞች ሄደው በማመልከታቸው እንዲሁም  ‘ሰውዬውን ከዚህ ክፍል ባታስወጡት፤ እዚህ ክፍል ውስጥ ችግር ይፈጠራል’ በማለት እስረኞች በጋራ ባሰሙት ጩኸት  የማረሚያ ቤቱ ሀላፊዎች ይባስን ከዚያ ክፍል አውጥተው  ወደ ሌላ ክፍል እንዳዛወሩት ተናግረዋል፡፡

 

አቶ አንዱዓለም አራጌ ቀደም ሲል ለፍርድ ቤት፦ “ይባስ የግድያ ሙከራ አድርጐብኛል፣ዶክመንቴንም ነጥቆ ለማን እንደሰጠብኝ አላውቅም፡፡ ዶክመንቴ እንዲመለስልኝ እንዲሁም  በደረሰብኝ ጉዳት  በቂ የህክምና ድጋፍ እንዳገኝ ይደረግልኝ”በማለት ያቀረበው አቤቱታ ተግባራዊ ምላሽ አለማግኘቱ ይታወቃል።

“የኢህአዴግን- እስረኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን  የማስደብደብ  እቅድ እየፈጸመ ነው” የሚባልለት  ይባስ አስፋው፤ ከኤች አይ ቪ /ኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በእስር ላይ የሚገኙትን የነጻነት ፋናዎች ለመርዳት የሚደረገው እንቅስቃሴ መቀዝቀዝ ፣ የእሰረኞችን ቤተሰቦች ማሳዘኑን ለማወቅ ተችሎአል። የኢሳት አዲስ አበባ ዘጋቢ የሶስት እስረኛ ቤተሰቦችን የፋሲካ በአል አከባበር ለማየት በቤታቸው በተገኘበት ወቅት ከእስረኞች ወላጆችና የትዳር ጓደኞች እንደተረዳው ፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእስረኞች ቤተሰቦችን በበቂ ሁኔታ አለመንከባከባቸው አሳዝኖአቸዋል። በአንዳንድ ወገኖች መጠነና ድጋፍ ቢደረግላቸውም፣ ከችግሩ ስፋት አንጻር የተደረገላቸው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን በሀዘን የገለጡ አንድ ወላጅ ፣ ልጃቸው ለአገሩ ነጻነት ሲል ህይወቱን ለመስጠት ሲወስን፣ በተሻለ የኑሮ ደረጃ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ቤተሰቡና እሱ በችግር እንዳይመቱ መንከባከብ ሲገባው ይህን ባለማድረጉ አዝነዋል። እስረኞች በሞራል ጠንካሮች እንዲሆኑ ማድረግ ከእያንዳንዱ ነጻነትን ከሚናፍቅ ሰው ሁሉ የሚጠበቅ እንጅ ለበተሰቦች ብቻ የሚተው አለመሆኑን እኝሁ እናት ተናግረዋል።

ተመሳሳይ አስተያየት የሰጠች የአንድ እስረኛ ባለቤትም፣ ባለቤቷ ከታሰረ ጀምሮ ከፍተኛ በሆነ ችግር ላይ መውደቋን ገልጣለች።

__________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide