ኢሳት ወደ አየር ተመለሰ

ግንቦት ፲ ( አሥር ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለአንድ ሳምንት ያክል የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ኢሳት ከአየር ላይ እንዲወርድ ለማድረግ የቻለ ቢሆንም፣ አስተዳዳሩ ባደረው ከፍተኛ ጥርት ወደ አየር ለመመለስ ችሎአል።
ሰሞኑን ሲደረግ የነበረው ሙከራ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት ኢሳት ሙሉ በሙሉ የ24 ሰአት አገልግሎቱን ጀምሯል።
ከ8 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት የኢሳትን ስርጭት ለማፈን የሚሞክረው ገዢው ፓርቲ፣ ሰሞኑን ኢሳትን ለሚያሰራጩ ኩባንያዎች ልዩ የቢዝነስ ስምምነት በማድረግ ኢሳትን ከእንግዲህ እንዳያስተናግዱ የማድረግ ዘመቻውን አጠክሮ ቀጥሎአል።
ፈተናው ከአቅም በላይ እየሆነ ቢመጣም አስተዳደሩ ያለውን የመጨረሻ አማራጭ ሁሉ ተጠቅሞ በአየር ላይ ለመቆየት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያኖች ኢሳት ሲቋረጥ የዘወትር ትብብራቸውን በመስጠት እንዲደግፉት አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል።
ስርጭታችንን AM6 በሚባለው ሳተላይት ላይ በ53 ዲግሪ የምስራቅ አቅጣጫ በማዞር፣ ፍሪኩዌንሲ ላይ 12719፣ ሲምቦል ሬት ላይ ደግሞ 27 ሺ 500 በመጻፍ የምታገኙት መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።