ኢሳት በሳተላይት የሬዲዮ ስርጭት ጀመረ

ኢሳት ዜና:- ኢሳት በቅርቡ የከፈተው የአጭር ሞገድ ስርጭት በኢትዮጵያ መንግስት መታፈን መጀመሩን ተከትሎ የሳተላይት የሬዲዮ ስርጭት በመጀመር የመንግስትን አፈና ለመቋቋም ወሳኝ እርምጃ ወስዷል።

የአጭር ሞገድ ስርጭቱ እየታፈነም ቢሆን እንደሚቀጥል የገለጠው ማኔጅመንቱ፣ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያውያን በሳተላይት ኢሳትን የሚስቡበት አማራጭ ቀርቦላቸዋል።

አዲሱ የሳተላይት ስርጭት በ ኤቢ 2 ሳተላይት፣ በስምንት ዲግሪ ዌስት በ11 ሺ 5 መቶ 95 ሞገድ ቨርቲካል በ27 ሺ 5 መቶ ሲምቦል ሬት በ ሶስት አራተኛ ኤፍ ሲ በኬ ዩ ባንድ ይተላለፋል።

ኢሳት አዳዲስና ከዚህ ቀደም የተላለፉ  ዝግጅቶችን በማደባለቅ ሳምንቱን በሙሉ ለ24 ሰአት የሚያቀርብ በመሆኑ አድማጮች የኢሳትን ዝግጅቶች በተለያዩ ሰአቶች ለመከታታል ያመቻቸዋል።

በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የኢሳትን አዲሱን ፍሪኩዌንሲ አገር ቤት ለሚገኙ ዘመዶቻቸው እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም በቅርቡ በሚጀመረው የገቢ ማሰባሰብ
ስራ ላይ እንዲሳተፉ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።

የመለስ መንግስት የኢሳትን ቴሌቪዥንና የራዲዮ ስርጭቶች ለማፈን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያወጣ ይታወቃል።

ኢሳት ለኢትዮጵያውያን  ነጻ መረጃዎችን በማቅረብ አሁን በመላ አገሪቱ የሚታየውን የመረጃ እጥረት ለመቅረፍ አልሞ የተነሳ የመገናኛ ብዙሀን ነው።

ኢሳት ቴሌቪዥን ከታፈነበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ ሺ የሚቆጠር የድጋፍ መልእክቶች ከኢትዮጵያና በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደርሶታል።

ኢሳት ከአጭር ሞገዱና ከሳተላይት ሬዲዮኖች በተጨማሪ የቴሌቪዥን ስርጭቱን ለመጀመርም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።