ኢህአዴግ በደንብ አስከባሪ ስም ያሰለጠናቸውን ከ1700 በላይ ሰዎች ሊያስመርቅ ነው

ግንቦት ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ የተለያዩ መረጃ የመሰብሰብ ስራዎችን እንዲሰሩለት ለወራት በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ሲያሰለጥናቸው የነበሩትን ከ1700 በላይ ሰልጣኞች ሰሞኑን ያስመርቃል።
ሰልጣኞቹ ከሁሉም የአዲስ አበባ ወረዳዎች የተውጣጡ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር ከገቡት 2 ሺ ሰልጣኞች መካከል 300 የሚሆኑት የተቃዋሚዎች አስተሳሰብ አለባችሁ በሚል ተገምግመው እንዲባረሩ ተደርጓል። በስልጠናው ወቅት የአገሪቱን ችግር እያነሱ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ ሰዎች፣ ተለይተው ከታወቁ በሁዋላ እንዲባረሩ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በከተማዋ ውስጥ የሚካሄደውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በመከታተል መረጃ እንዲሰጡ እንዲሁም በገዢው ፓርቲ በኩል ሆነው የሚሰጣቸውን ማንኛውንም አይነት ስራ እንዲፈጽሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
ሰልጣኞቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ደንብ አስከባሪዎች ተብለው የሚመደቡ ቢሆንም፣ ዋናው ስራቸው መረጃዎችን እየተከታተሉ ለደህንነት ክፍሉ ማቅረብ ነው። አብዛኛው ስልጠና መረጃዎችን በመሰብሰብ የሚሰጡ ትእዛዛዝትን በቅንነትና በታማኝነት መተግበር ላይ ያተኮረ ነበር።
በስልጠናው ላይ በመሳተፍ ላይ ያለ አንድ ግለሰብ እንደተናገረው፣ አብዛኛው ወጣት የእንጀራ ጉዳይ ሆኖበት እንጅ በስልጠናው አምኖበት እየተሳተፈ አለመሆኑን ገልጾ፣ የስልጠናው ዋና አላማ መረጃዎችን ለመንግስት እየሰበሰቡ ማቅርብ ነው ብሎአል።