አዲስ የተሾሙት አመራሮች በቡድን ተደራጀው በህዝብ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ሚያዝያ ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ እየተመደቡ ያሉ አመራሮች በቡድን ተደራጅተው በህብረተሰቡ ላይ ችግሮችን በመፍጠር ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት የአዴት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እማመይ አለባቸው፣ ከቀበሌ ሁለት አመራር ጀምሮ እስከ ከንቲባው ድረስ ህዝብን በማመስ ማስቸገር እንጅ ምንም አይነት ስራ ሲሰሩ አይታዩም ይላሉ። ከአሁን በፊት በብአዴን አባልነት ይሳተፉ እንደነበር የገለጹት ቅሬታ አቅራቢ ስርዓቱ ሙሰኝነት የተንሰራፋበት በመሆኑ በዚህ ምክንያት ከፓርቲው አባልነት ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል፡፡
“ወጣቱ እየታፈነ ነው” በማለት ቅሬታውን ያቀረበው ወጣት በርካታ ወጣቶች በተለያዩ ምክንያት እየታሰሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ወጣቱ ልዩ ልዩ ሃሳቦችን በስብሰባ የሚያቀርቡት ሁሉ እየተለቀሙ ወደ አስርቤት በመጋዝ እና ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ እስከ አንድ አመት ተፈርዶባቸው እየታስሩ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢው ተናግሯል፡፡
የከተማው የፖሊስ ሃይል ከፍተኛ ክራይ ሰብሳቢ እንደሆነ የተናገረው ወጣት ፖሊሶች ውሏቸውን በቻይና መንገድ ስራ ድርጅት በማድረግ ግለሰቦች ጠባቂ እስከ መሆን መድረሳቸውን ገልጿል፡፡ በዚህ አድራጎታቸው ከቻይናዎች ጋር በመመሳጠር መኖሪያ ቤታቸውን ከድርጅቱ በወጣ ሲሚንቶ የገነቡ የፖሊስ አመራሮች መኖራቸውን አጋልጧል፡፡
በሚካሄዱ ስብሰባ በመገኘት አመራሮችን እንዳያጋልጥ በርካታ ነዋሪዎች መታሰራቸውን የተናገረው ቅሬታ አቅራቢ፣ የከተማው ፖሊስ እንዳንናገር ከማፈን ውጭ ህዝብ የሚጠቅም ስራ አይሰራም ይላል። ገዢው ፓርቲ ከህዝባዊ አመጹ በሁዋላ በተለያዩ ወረዳዎች ባለስልጣኖችን ቢሾምም፣ ህዝቡ አሁንም ቅሬታውን ከማቅረብና የለውጥ ጥያቄ ከመጠየቅ አልተቆጠበም።