አዲስ አበባ ውስጥ የታሰሩ የግብጽ ዜጎች ተፈቱ

ጥር ፬ (አራት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ከተነሳው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ጋር በተያያዘ ለወራት በእስር ላይ የነበሩ ሶስት ግብጻዊያን ዜጎች ከእስር መስፈታታቸውን የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት አስታወቀ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ከተገደሉበት የኢሬቻ እልቂት በኋላ ካለምንም ጥፋታቸው በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ምንም ዓይነት ክስ ያልቀረበባቸው መሆኑንም መግለጫው አትቷል። ሶስቱም ግብጻዊያን በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ጥረት ረቡዕ እለት ምሽት ላይ በነጻ እንዲለቀቁ ተደርገው ከአዲስ አበባ ወደ ካይሮ መግባታቸው ታውቋል።

ከሶስት ወር በፊት የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ሳማ ሽኩሪ ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ሶስቱ ግብጻዊያንን ለማስለቀቅ ከአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል። እ.ኤ.አ. 2016 ኦክቶበር ወር ላይ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ማእበል አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስት የግብጽ እና የኤርትራ መንግስት እጅ አለበት በማለት ክስ ሲያቀርብ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ያለውን የመሬት ቅርምት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደ ውጪ ሃይሎች በማሳበብ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱንም ሚንስትር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የግብጽን መንግስት ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ ገዢው ፓርቲ  ያቀረበውን ውንጀላ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ውድቅ አድርገውታል። ”የግብጽ መንግስት ለተቃዋሚ ኃይሎች በፍጹም በጭራሽ ምንም ዓይነት እገዛ አላደረገም አያደርግምም። በኢትዮጵያ ላይ የምንፈጽመው ምስጢራዊ የሆነ ተልእኮ የለንም።” ሲሉ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ በወቅቱ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።