አዲሱ የሊዝ አዋጅ በክፍለ ሀገራት ሳይቀር ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋት ፈጥሯል

ጥር 23 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደዘገቡት፣ የኑሮ ውድነቱ የፈጠረው ውጥረት ሳይበርድ አሁን ደግሞ የሊዝ አዋጁ መጨመሩ ህዝቡ አለመረጋጋት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በኦሮሚያ የሚኖሩ ሰው ሲናገሩ በእርሳቸው አካባቢ አዲሱ የመሬት ፖሊሲ የህዝብ አለመረጋጋት እየፈጠረ ነው።

ነገሮች ሊፈነዱ ተቃርበዋል የሚሉት እኝሁ ግለሰብ መድረክ የሊዝ አዋጁን በመቃወም ሊጠራ ያሰበው ስብሰባ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘቱንም ገልጠዋል።

በደቡብ የሚኖሩ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ አንድ ሰውም እንዲሁ የሊዙን ፖሊሲ ህዝቡ እየተቃወመው ነው።

ከየአቅጣጫው የሚሰማው ተቃውሞ የመንግስት ባለስልጣናት እርስ በርስ የሚቃረን መግለጫ እንዲሰጡ እያስገደዳቸው እና ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸው ታውቋል።