አኤሳዋን  የስፖርት ማህበር የ2017 ፕሮግራሞቹን ለመሰረዝ ተገደደ

ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2009)

በሰሜን አሜሪካ “የሃገር ውስጥ ገቢ ህግ” መሰረት ትርፋማ ባልሆነ እና ከታክስ ነጻ በሆነ መልኩ ከ2011 ጀምሮ የተቋቋመው “አኤሳዋን” የስፖርት ማህበር የ2017 ፕሮግራሙን ለመሰረዝ መገደዱን የቀድሞ የስፖርት ማህበሩ አመራሮች ለኢሳት ገለጹ።

እነዚሁ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቀድሞ የስፖርት ማህበሩ አመራሮች “አኤሳዋን” ላለፉት አምስት አመታት ያካሄደው ፕሮግራም በዝግጅቶች እጥረት ድርቅ በመመታቱና ታዋቂ ድምጻውያን የኪነጥበብ ሙያተኞች በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አመራሮቹ አያይዘው እንደገለጹት ከሆነ በ”ኤሳዋን” ውስጥ የተፈጠረው ቤተሰባዊ አመራር ድርጅቱ ተጠያቂነት የጎደለውና የገንዘብ ምንጩና አጠቃቀሙ ላይ ህጋዊ አሰራሩ ባልተከተለ መልኩ እንዲፈጸም ማድረጉን ተናግረዋል። ይህም የስፖርት ማህበሩን በየአመቱ ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስፖንሰር ሲያደርጉ የነበሩትን ቱጃሩ ሼህ መሃመድ አላሙዲንን ማበሳጨቱንና የዘንድሮው ዝግጅት ስፖንሰር እንደማያደርጉ መናገራቸውን የውስጥ መረጃዎች አመላክተዋል።

የ”ኤሳዋን” ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀል፣ እንዲሁም ወንድማቸውንና የማህበሩ ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ብስራት ገብረመስቀል የስፖርት ዝግጅቶቹ በህዝብ ድርቅ የመመታታቸው ምክንያት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) በሰራው ቅስቀሳ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ይህ “አኤሳዋን” የተባለው ቡድን በቅድሚያ ዋናውን የስፖርት ፌዴሬሽን ESFNAን ለመሰንጠቅና ለመጠቅለል ያደረገው እንቅስቃሴ በመክሸፉና በፍ/ቤትም በመረታቱ በአዲስ ስያሜ ለመንቀሳቀስ መገደዱን ማስታወስ ተችሏል።