አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው አቶ ተስፋዬ ሳህሉ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 24/2009)አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው አቶ ተስፋዬ ሳህሉ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሳምንታዊው የሕጻናት ፕሮግራም ላይ ከ40 አመታት በላይ በማዝናናትና በማስተማር ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው አባባ ተስፋዬ ሕይወታቸው ያለፈው እሁድ ሐምሌ 23/2009 መሆኑም ታውቋል።
ሰኔ 20 ቀን 1916 በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር ኮዳ በተባለ ቦታ የተወለዱትና በ94 አመታቸው ይህችን አለም የተሰናበቱት አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው አቶ ተስፋዬ ሳህሉ እጅግ ከታወቁበትና ከሚወደዱበት የህጻናት የቴሌቪዥን ፕሮግራም በተጨማሪ በልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ስራዎችም ይታወቃሉ።
በድምጻዊነት እንዲሁም በመድረክ መሪነት በኪነጥበባዊ ስራም ውስጥ ረዥም አመታት ያገለገሉት አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው አቶ ተስፋዬ ሳህሉ ከቴሌቪዥን የህጻናት ፕሮግራም በተጨማሪ እጅግ ታዋቂ የሆኑት በመድረክ ተውኔቶች እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
የአዛውንቶች ክበብ፣ኦቴሎ፣ሀሁ በስድስት ወር፣አሉላ አባነጋ፣ኤዲፐስ ንጉስ፣ዳዊትና ኦርዮን ከስራዎቻቸው ተጠቃሾች ናቸው።
አባባ ተስፋዬ በሚባለው ልዩ መጠሪያቸው የሚታወቁት አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው አቶ ተስፋዬ ሳህሉ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ሳምንት የክብር ዶክትሬት እንደሰጣቸውም ታውቋል።