አንድ ፖሊስ ጥር 21 ቀን የአስቴርዮ ማርያም ክበረ በዓል በሚከበርበት ዕለት በህዝቡ ላይ በተኮሰው ጥይት ጉዳት ደረሰ

ጥር 23 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጋሞጎፋ ዞን በጨንጫ ወረዳ አንድ የወረዳው ፖሊስ የአስቴርዮ ማርያም ክበረ በአል በሚከበርበት እለት በህዝቡ ላይ በተኮሰው ጥይት አንድ ሰው ወዲያውኑ ሲሞት ፣ በርካቶች በጽኑ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸው ታወቀ

የኢሳት የጋሞጎፋ ዞን ወኪል እንደዘገበው በጨንጫ ወረዳ የአስቴርዮ ማርያም በአል ከፍተኛ ህዝብ ተገኝቶ የሚያከብረው ሀይማኖታዊ ክብረ በአል ነው።

በእለቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከአርባምንጭ እና ከሌሎች ከተሞች የተሰባሰቡ ሰዎች በአሉን በሚያከብሩበት ወቅት ፣ የወረዳው ፖሊስ አባል ምክንአቱ ባልታወቀ ሁኔታ መሳሪያውን አንስቶ ወደ ህዝቡ በመተኮሱ አንድ ሰው ወዲያኑ ተገድሎአል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በጽኑ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።

ከፍተኛ የሆነ የህዝብ መተራመስ ተፈጥሮ እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጧል። ፖሊሱ በምን ምክንያት ሊተኩስ እንዳልቻለ ለማወቅ ባይቻልም፤ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ለማወቅ ተችሎአል።

ሀይማኖታዊ በአሉን ለማክበር የተገኘው ህዝብ አጋጣሚውን በመጠቀም በመንግስት ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል።

ተኳሹ ፖሊስ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሆኑ እንደታወቀ ህዝቡ የአካባቢውን ባለስልጣናት በሰላም ተከባብረን እና ተቻችለን በምንኖርበት አገር እርስ በርስ ልታጋጩን አትሞክሩ በማለት ሲቃወም ነበር።

በጨንጫ ወረዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመሬት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው አለመረጋጋት እንደቀጠለ መሆኑን ዘጋቢአችን ገልጧል።