አንድ የአሜሪካ ተቋም ከአምልኮ ጋር በተያያዘ በሳውዲ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ጠየቀ

የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአሜሪካ አለማቀፍ የሀይማኖት ነጻነት አስጠባቂ ተቋም ባወጣው መግለጫ የሳውዲ አረቢያ መንግስት እስረኞችን ያሰረበትን ትክክለኛ ምክንያት ይፋ እስካላደረገ ድረስ፣ መልቀቅ አለበት ብሎአል።

እስረኞቹ በእስር ቤት ውስጥ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን፣  የእስልምና ሀይማኖትን እንዲቀበሉ እየተገደዱ መሆኑን ድርጅቱ አክሎ ገልጧል።

35 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የታሰሩት ሴቶችና ወንዶች በአንድ ላይ በመሆን አምልከዋል በሚል ምክንያት ነው። ሳውዲአረቢያ የቤተሰብ አባል ያልሆኑ ሴቶችና ወንዶች በአንድ ክፍል ውስጥ መገኘታቸውን ትከለክላለች።

የሳውዲ መንግስት ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገራቸው ለመላክ ተዘጋጅቷል መባሉ አለማቀፍ ተቃውሞ እንደቀሰቀሰ ይታወሳል።