አንድ እስራዔላዊ የግርዛት ባለሙያ ተማሪዎቻቸው በኢትዮጵያና በሱዳን ህጻናት ላይ ልምምድ እንዲያካሄዱ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተጋለጠ

ኢሳት (ህዳር 21 ፥ 2009)

በእስራዔል አገር የግርዛት ትምህርትን በመስጠት የሚታወቁት አንድ የሃገሪቱ አንጋፋ ባለሙያ ትምህርት የሚሰጧቸው በርካታ ተማሪዎች በኢትዮጵያና በሱዳን ህጻናት ላይ ልምምድ እንዲያካሄዱ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተጋለጠ።

የሃገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው በአንድ ታዋቂ የምርመራ ጋዜጠኛ በድብቅ የተደረገው የቪዲዮ ቃለ-ምልልስ ተግባራዊ ሆኖ ከሆነ ድርጊቱ እጅት አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

በዘርፉ የ33 አመት የስራ ልምድ ያላቸው መምህሩ ኤሊያሁ አሱሊን የእስራዔሉ ኒው ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እርሳቸው ሳያውቁ ባካሄደባቸው ምርመራ ድርጊቱን ሆን ብለው ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።

የግርዛት የህክምና አገልግሎት በመስጠትና በማስተማር የሚታወቁት መምህሩ ለበርካታ ተማሪዎቻቸው ህገወጥ የሙያ ማረጋገጫን በመስጠት ተማሪዎቹ በኢትዮጵያና ሱዳናውያን ህጻናት ላይ የግርዛት ልምምድ እንዲያካሄዱ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ምርመራውን ላካሄደው ጋዜጠኛ አስረድተዋል።

ጋዜጠኛው መምህሩ ለምን በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንዲህ ያለ ተግባርን እንደሚፈጽሙ በጠየቃቸው ጊዜ “በነሱ ላይ የፈለከውን ነገር ብታደርግ የሚረዱትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር የለም” ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።

በእስራዔል መገናኛ ብዙሃን በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ሆነው የሚገኙት መምህር አሱሊን “ሁሉም እኮ ወደ ኢትዮጵያውያኑና ሱዳናዊያኑ ጋ የሚሄደው ለመማሪያ ሲል ነው በማለት አክለው ተናግረዋል።

ጸያፍ ቃላትን በመጠቀም ተማሪ መስሎ ለቀረባቸው ጋዜጠኛ ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩት መምህሩ፣ ተማሪዎቹን ለማስተማር በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ያስከፍሉ እንደነበር ታይምስ ኦፍ እስራዔል የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

መምህሩ የግርዛት ስልጠናውን ለመስጠት ከአንድ ተማሪ 11ሺ ዶላር ያስከፍሉ የነበረ ቢሆንም፣ ለምን ያህል ተማሪዎች በዚህ መልኩ ስልጠናን ሰጥተው እንደነበር የታወቀ ነገር የለም።

መነጋገሪያ ሆኖ የሚገኘውን ድርጊት ስለመፈጸማቸው የቪዲዮ ማብራሪያን ሰጥተው የነበሩት መምህር አሱሊን ለህዝብ ይፋ የሆነው የቪዲዮ ቃለ-ምልልስ በሚኖሩበት የሃዴራ ከተማ በፖለቲካ አባላት ሆን ተብሎ የተቀነባበረባቸው ቪዲዮ እንደሆነ ቪዲዮው ኤዲት ተደርጓል ሲሉ ምላሽን ሰጠዋል።

ለበርካታ አመታት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህጻናት የግርዛት አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር የሚናገሩት ባለሙያዎች ስራቸውን እንደተቀደሰ ስራ እንደሚያዩት አክለው አስታውቀዋል።

የምርመራ ስራውን ያካሄደው የእስራዔሉ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ተመሳሳይ ባለሙያዎች ድርጊቱ በመፈጸም ላይ መሆኑን በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ጉዳዩን በተመለከተ የእስራዔል መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

ነዋሪነታቸው በእስራዔል የሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት የዘረኝነትና የተለያዩ በደሎች ይደርሱብናል በማለት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።