አቶ ያረጋል አይሸሹም ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በሁዋላ በቁም እስር ላይ እንደሚገኙና ንብረታቸውን ካስረከቡ በሁዋላም ወደ ወህኒ እንደሚወርዱ ታወቀ

ኢሳት ዜና :- የቀድሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ ያለመከሰስ መብታቸውን ፓርላማው አንስቷል፡፡

አቶ ያረጋል የተነሱት የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ከተቀበለው በሁዋላ ነው።
አቶ ያረጋል የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ በክልሉ እንዲሠሩ በጀት ከተያዘላቸው ሦስት ትምህርት ቤቶች ላይ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጋር በመመሳጠር ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በማስረጃ በመረጋገጡና በቂ አመላካች ነገሮች በመኖራቸው መሆኑ ተጠቅሷል

በአሁኑ ጊዜ በቁም እስር ላይ የሚገኙት አቶ ያረጋል የያዙትን የመንግስት ንብረት ካስረከቡ በሁዋላ ወደ እስር ቤት ይወርዳሉ።

ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያቁ የሚናገሩት ገለሰቦች እንደሚሉት አቶ ያረጋል የታሰሩበት ዋና ምክንያት ፖለቲካዊ ነው።

ግለሰቡ የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ህወሀት በክልላቸው የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት አጥብቀው በመቃወም፣ በእነ አቶ አባይ ጸሀዬ የተመራ ቡድን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር።

ከማስጠንቀቂያው በሁዋላ አቶ ያረጋል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የመንግስት ተቃዋሚዎችን ይደግፋሉ የሚል ክስ ቀርቦባቸው  ከፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ ተደርጓል።

አቶ ያረጋል የመንግስት አካሄድ አላስደስታቸው በማለቱና ለደህንነታቸውም ስለሰጉ ወደ ካናዳ በመሄድ ጥገኝነት ለመጠየቅ ሙከራ አድርገው ነበር። ይሁን እንጅ ጉዳያቸው እያለቀ በነበረት ጊዜ ፣ ጉዳዩን ይከታተሉላቸው የነበሩትን ግለሰቦች ሳያማክሩ  ተመልሰው ሄደዋል።

መንግስት ግለሰቡ ወደ አገር ቢመለሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ በፈጸሙት ወንጀል  እንደማይጠየቁ ና በፌደራል መንግስቱ ስር ባሉ መስሪያቤቶች እንደሚሾሙ ካግባባ በሁዋላ፣ በመጨረሻም ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳት ለእስር ዳርጎዋቸዋል።

አቶ ያረጋል ከእርሳቸው ጋር በቅርብ ይገናኙ ለነበሩ ሰዎች “ስደትን ህይወት አልለምደውም፤ ጉዳየም ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል” በማለት መናገራቸውንና በተለይም የቤተሰባቸው ሁኔታ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ጉዳዩን በቅርበት ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች ገልጠዋል።

አቶ ያረጋል በሙስና ቢጠረጠሩ ኖሮ ቀድሞውንም ወደ አገር ቤት አይመለሱም ነበር የሚሉት የቅርብ ሰዎች፣ መንግስት በሙስና ሰበብ አድርጎ ሊያስራቸው ቢፈልግም ዋናው መንስኤ ግን የፖለቲካ ልዩነት የፈጠረው ነው ይላሉ።

በአሁኑ ጊዜ የቤንሻንጉል ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው የሚያገለግሉት ግለሰብ ለህወሀት አመራሮች ታማኝ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።