አቶ ከፍያለው አዘዘ እንደወጡ የቀሩት፤ ለስራ ወደ ዱባይ ከተላኩ በኃላ መሆኑን ሪፖርተር ዘገበ

መስከረም ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩትና፤ ስርአቱን ከድተው አሜሪካ የገቡት አቶ ከፍያለው አዘዘ እንደወጡ የቀሩት፤ ለስራ ወደ ዱባይ ከተላኩ በኃላ መሆኑን ሪፖርተር ዘግቧል።

አቶ ከፍያለው አዘዘ ወደ አሜሪካ መኮብለላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በመረዳቱም መኪናቸውን መረከቡንና፤ ስለ አቶ ከፍያለው መረጃ አልሰጠህም የተባለው ሹፌራቸውም ያለስራ እንዲቀመጥ መደረጉን ከሪፖርተር ዘገባ መረዳት ተችሏል።

የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ለሚገነባው ቴሌቭዥን ጣቢያ፤ ዕቃ ለመግዛት ወደ ዱባይ ከተላከው ቡድን ጋር አብረው የተጓዙት አቶ ከፍያለው አዘዘ፤ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ርሳቸው ወደ አሜሪካ መሻገራቸውና በዚያው መቅረታቸው ታውቋል።

የብአዴን አባል የሆኑት አቶ ከፍያለው አዘዘ ከመክዳታቸው በፊት ከምክትል ከንቲባነት  ተነስተው ነበር።

ኢሳት የአቶ ከፍያለው አዘዘን መክዳት ከቀናት በፊት መዘገቡም ይታወሳል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕውሀት) ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የቀድሞ የገቢዎች ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው በላይ ስርአቱን ከድተው አሜሪካ መግባታቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን አይዘነጋም።

በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ የተሳካ ውይይት አደረጉ።

በእየሩሳሌም በተካሄደና “ኢትዮጵያን እናድን አንድነት ማህበር በእስራኤል” የተሰኘ ድርጅት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ፤ በስደት በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሲኖዶስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑትለ፤ አቡነ መቃርዮስና የአይሁድ እምነት ቤተእስራኤላዊ ራቢ ያፌት አለሙ በእንግድነት ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ስብሰባ ላይ፤ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፤ ስለኢትዮጵያና ስለማህበረሰባቸው ችግሮች ተወያይተዋል።

የስብሰባው መሪ አቶ ሳሙኤል አለባቸው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ የገዢውን ፓርቲ ደጋፊዎች ጨምሮ የተለያየ አመለካከት ያለቸው ኢትዮጵያዊያን በስብሰባው እንዲሳተፉ ጥሪ ቢያደርጉም፤ ስብሰባውን በቪዲዮ ለመቅረጽ የሞከሩ የገዢው መንግስት ደጋፊዎች በፈጠሩት ትርምስ የተነሳ ከአዳራሹ በፖሊስ ተገፍተው እንዲወጡ ተደርገዋል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በእስራኤል በእስር ቤቶች የሚገኙትን በመቶዎች የሚቆጠሩትን ኢትዮጵያዊያን ለማስፈታት ጥረት እንደሚያደርጉም ሁለቱ የሀይማኖት መሪዎች ቃል እንደገቡ አቶ ሳሙኤል ለኢሳት ገልጸዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide