አቶ አባዱላ ገመዳ ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት በድርጅታቸውና በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ይሁንታ መሆኑን ገለጹ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 6/2010) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት በድርጅታቸውና በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ይሁንታ መሆኑን ገለጹ።

የትልቅ ስልጣን ባለቤት ሆኜ የሕዝቤና የድርጅቴ ጥቅም ሲነካ ማየቱ ተገቢ ባለመሆኑ ርምጃውን ወስጃለሁ ሲሉ ለኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን ገልጸዋል።

የስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ከአንድ ሳምንት በፊት ያረጋገጡትና አሁንም በሃላፊነታቸው ላይ የሚገኙት አቶ አባዱላ ገመዳ ስልጣን ለመልቀቅ የተገደዱበትን ምክንያት መልቀቂያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ እንደሚናገሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

አሁንም መልቀቂያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ለኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን ምክንያታቸውን ተናግረዋል።

የድርጅታችንንና የሕዝቡን መብትና ክብር የሚያጓድል ነገር እያዩ ያንን ተሸክሞ ከመቀጠል ከስልጣን በመልቀቅ ነገሩን ለማስተካከል መስራት ይገባል በሚል መልቀቂያ ማቅረባቸውን አቶ አባዱላ ገመዳ ተናግረዋል።

ይህም በድርጅቱ ኢህአዴግና በድርጅቱ ሊቀመንበር ሃይለማርያም ደሳለኝ ይሁንታ የቀረበ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ መሆኑን አብራርተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ለኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን በሳምንቱ መጨረሻ በኦሮምኛ ቋንቋ በሰጡት በዚህ ማብራሪያ በሀገር ውስጥና በውጭ ያለውን የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ወደ ኢኮኖሚ ልማት መለወጥ እንደሚገባም በቃለምልልሱ ወቅት አንስተዋል።

ቀሪ ጊዜያቸውን ከኦህዴድና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል ያለው የሰላም እጦት የክልሉን መንግስት አቅም ያዳክማል በማለት የተናገሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባም መክረዋል።