አቶ በረሃነ ገ/ክርስቶስ የኢሕአዲግ አባላት ከሆኑት ዲፕሎማቶች ጋር ተወዛገቡ

ህዳር ፲፭ (አስራ አምት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሚኒስትር አቶ በረሃነ ገ/ክርስቶስ የኢሕአዲግ አባላት ከሆኑት ዲፕሎማቶች ጋር መወዛገባቸውን የቅርብ ምንጮችን የጠቀሱ ዘገባዎች ይፋ አድርገዋል የውዝግቡ መነሻ የኢሕአዲግ አባላት ያልሆኑ ዲፕሎማቶች ለስራ በመታጨታቸው ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተጠባባቂ ሚንስትር  አቶ በረሃነ ገ/ክርስቶስ ከምክትላቸው ከአቶ ነጋ ፀጋዬ ጋር በመሩት ሥብሰባ ላይ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻል ደረጃ የኢሕአዲግ አባላት የሆኑ ዲፕሎማቶች የተገኙበት መሆኑም ተመልክቷል። ለውዝግቡ መነሻ የሆነው የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ለቀመንበርነት ተረኛ ኢትዮጲያ ከመሆኗ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ለቀመንበርነት ቦታ በመጪው ጥር ኢትዮጲያ እንደምትቀበል በመረጋገጡ ይህንን ኋላፊነት ለመወጣት የማስተባበሩን ሥራ የሚሰሩት አንጋፋዋ ዲፕሎማት ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ረዳት እንዲሆኗቸው ሦስት ዲፕሎማቶችን ይጠቁማሉ አምባሳደሯ የጠቆሟቸው ሦስቱ ግለሰቦች የፓርቲ አባላት አለመሆናቸው የኢሕአዲግ አባላት የሆኑ ዲፕሎማቶችን አስቆጥቷል።

አምባሳደር በረሃነ ገ/ክርስቶስ የአንዳፋዋን ዲፕሎማት አስተዋፅኦ በመዘርዘር ስለ አስፈላጊነታቸው ሲያነሱ ይበልጥ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ስብሰባውን በፈለጉት ሠዓት ለመጨረስ እንኳን ከተሰብሳቢው እንዳልተፈቀደላቸው የተገኘው ዜና ያብራራል መስሪያ ቤቱን የመምራት ብቃት የለህም እስከመባል መድረስም ተመልክቷል።

ከምርጫ 97 በኋላ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ዲፕሎማቶች መስሪያ ቤቱን ጥለው በመሄዳቸው ከ 200 በላይ የኢሃዲግ አባላት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ውጭ ጉዳይን መቀላቀላቸውን መረዳት ተችሏል።

አምባሳደር ቆንጅት ሥነ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ህብረት እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጲያ አምባሳደር ናቸው ከንጉሡ ግዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።