አቶ በረከት ስምኦን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 6/2010)ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነት እንዲነሱ የተወሰነባቸው አቶ በረከት ስምኦን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማቅረባቸው ተሰማ።

ላለፉት ሰባት አመታት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ሲሰሩ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን የፖሊሲ ምርምርና ጥናት ማዕከል በተባለው ተቋም የአቶ አባይ ጸሀዬ ምክትል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት ዛሬ እንደዘገበው አቶ በረከት ስምኦን የስራ መልቀቂያ ያቀረቡት ይሰሩበት ከነበረው የፖሊሲ ምርምርና ጥናት ማዕከል ነው።

እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ሀሙስ በስራቸው ላይ እንደነበሩ የተገለጸው አቶ በረከት ስምኦን የስራ መልቀቂያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ማቅረባቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነቱንም ለሌላው የብአዴን አባል ዶክተር ይናገር ደሴ እንዲያስረክቡ የተወሰነባቸው አቶ በረከት ስምኦን የስንብት ደብዳቤው የደረሳቸው ከመንግስት የፋይናንስ ተቋማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንደሆነም ተመልክቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ መልቀቂያ ባቀረቡ ማግስት የአቶ በረከት መልቀቂያ መከተሉ በኢህአዴግ ውስጥ ቡድናዊ እንቅስቃሴ ለመኖሩ አመላካች እንደሆነ የሚገልጹት የፖለቲካ ተንታኞች በቀጣይ ተጨማሪ ርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉም ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል።